በጢሻ ውስጥ ተደብቀው በነበሩ 250 የነዳጅ ቦቴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

20 Hrs Ago 115
በጢሻ ውስጥ ተደብቀው በነበሩ 250 የነዳጅ ቦቴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አለአግባብ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ከ10 እስከ 15 ቀናት በጢሻ ውስጥ ተደብቀው በነበሩ 250 የነዳጅ ቦቴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
 
ከነዳጅ ምርቶች ስርጭትና ግብይት ጋር ተያይዞ በሚስተዋሉ ሕገወጥ ተግባራት ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም አስታውቋል።
 
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ከሰሞኑ አለአግባብ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ከ10 እስከ 15 ቀናት በጢሻ ውስጥ ተደብቀው በነበሩ 250 የነዳጅ ቦቴዎች ላይ ቅጣት መጣሉን ገልጸዋል።
 
በዚህም ቦቴዎቹ ለስድስት ወራት ምንም አይነት የነዳጅ ምርት እንዳያዘዋውሩ ታግደዋል። በዚህ ሕገወጥ ተግባር ተባባሪ የነበሩ 19 ማደያዎችም ለስድስት ወራት ከግብይቱ መታገዳቸው ተገልጿል።
 
ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸውም ጠቅሰዋል።
 
35 ማደያዎች ተመሳሳይ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል።
 
385 ሺህ ሊትር ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተወርሶ 27 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
 
በቀጣይ ከዲጅታል የግብይት ሥርዓት ውጭ ግብይት የሚፈጽሙ ማደያዎችን ከንግድ ሥርዓቱ የማስወጣት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል።
 
ሚኒስትሩ መንግስት እየወሰደ ያለው ጠንካራ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
 
በሌላ በኩል፤ ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት 137 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ጥቅል የነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
 
ከጥቅል ድጎማው ውጪ የህዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻና የከተማ አውቶብሶችን ታሳቢ ላደረገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ባለፉት ስድስት ወራት 463 ሚሊዮን ብር መንግስት ድጎማ ማድረጉን አንስተዋል።
 
በወንድወሰን አፈወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top