በፓሪስ ኦሊምፒክ የተወዳደሩ አትሌቶች የተሸለሟቸው ሜዳሊያዎች በፍጥነት እየተበላሹ በመሆኑ በሌላ እንዲተካላቸው እየጠየቁ ነው ተብሏል፡፡
33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከተካሄደ 5 ወራት ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ለአሸናፊ አትሌቶች የተበረከቱት ሜዳሊያዎችም በንድፋቸው ልዩ እና ዘመናዊ መልክን ያካተቱ እንደነበሩ ተነግሯል።
ነገር ግን አሶሼትድ ፕረስ ባወጣው ዘገባ ሜዳሊያዎቹ አሁን ላይ የጥራት ጥያቄ እንደተነሳባቸው ነው የተገለጸው።
ከ100 በላይ አትሌቶች ሽልማታቸው መበላሸቱን በማህበራዊ ገፆቻቸው ላይ ማሳየታቸውን ተከትሎ የሜዳሊያዎቹ በአጭር ወራት ውስጥ መበላሸት ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።
አትሌቶች የተሸለሙት ሜዳሊያ ጥራት ቅር እንዳሰኛቸውም ዘገባው ጠቁመዋል።
ሜዳሊያዎቹ በመልካቸው፣ በጥንካሬያቸው እና በንድፋቸው ላይ ችግሮች እንደተገኙባቸው ነው የተገለፀው።
ይህንንም ተከትሎ የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጅ ኮሚቴ በሜዳሊያዎቹ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመገምገም እና የጉዳቱን መንስኤ ለመረዳት የሜዳሊያዎቹን የማምረትና የጥራት ቁጥጥር ኃላፊነት ካለው ሞናይ ዴ ፓሪስ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ማስታወቁ ተነግሯል።
በሴራን ታደሰ