የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
12ኛው የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጉባኤ በጋምቤላ ክልል በመካሄድ ላይ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲጎለብት የሚያስችሉ የሕግና ተቋማዊ ሪፎርሞች መካሄዳቸውን ገልፀዋል።
በሪፎርሙም መንግስት ለሲቪል ማህበራት መብትን የሚያጎናፅፍ ሕግ አውጥቶ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረጉም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።
የሲቪል ማህበራትም የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ከመንግሥት አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት በመስራት ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው በታማኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አፈ ጉባኤው አሳስበዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሲቪል ማህበራት ለሀገር ልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።
ካሁን ቀደም የነበረው የተዛባ ግንኙነት ታርሞ አሁን ላይ በመንግስትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሀከል በትብብርና በቅንጅት መርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖር መደረጉንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፤ በሪፎርም ሂደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድሮጅቶች እንቅስቃሴ የበለጠ ተጠናክሮ በተጨባጭ የህዝብን ኑሮ እንዲያሻሽል ለማስቻል ባለስልጣን መስርያ ቤቱ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በሕግና በተቋቋሙለት ዓላማ መሰረት በመንቀሳቀስ የህዝብን ጥቅም የሚያረጋግጡ ተግባራትን ሊያከናውኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ገልፀዋል።