የተፋሰስ ልማት ተግባራትን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ መጥቷል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

13 Hrs Ago 81
የተፋሰስ ልማት ተግባራትን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ መጥቷል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
የተፈጥሮ ሐብት ልማት ግብን ለማሳካት በየዓመቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ መጠነ ሰፊ የተፋሰስ ልማት ተግባራትን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ መምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሀገራዊ ንቅናቄን አስጀምረዋል።
 
የተፋሰስ ልማታችንን በማስፋት የአፈር ሐብታችንን ለብልጽግናችን ለማዋል መረባረብ አለብን ሲሉም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስገንዝበዋል፡፡
 
የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብትና የተፋሰስ ልማትን በመተግበራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ቁርጠኝነታችንን አሳይተናል ብለዋል።
 
በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎች ማገገማቸውን፣ የአፈር መከላት መቀነሱን እና የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን አብራርተዋል፡፡
 
አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማቶችን በመጠበቅና በባለቤትነት በመያዙ የንብ ማነብ፣ የእንስሳት ርባታ፣ የመስኖ ልማት እና የፍራፍሬ ልማትን በመተግበር ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በዘርፉ እስከ አሁን ያስመዘገበችው ስኬት፤ በመንግሥት አመራር፣ በሞያተኞች፣ በኅብረተሰቡና በልማት አጋሮች ተሳትፎ የተገኘ ድምር ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
በዚህ ዓመት በ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት እንደሚካሄድም አመላክተዋል፡፡
 
ይህን በማሳካትም አፈራችንን ለብልጽግናችን ለማዋል ሁሉም አካላት በትጋት እንዲረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top