የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስትና የህዝብ ንብረትን ለማስመለስ የነበረውን የሕግ ክፍተት የሚሞላ የንብረት ማስመለስ አዋጅን አጽቋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው14ኛ መደበኛ ስብሰባው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
አዋጁ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈራን ንብረት ማስመለስ የሚያስችሉና የሕግ-ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ በረቂቅ አዋጁ የተደረጉ ማስተካከያዎችና የተጨመሩ አንቀጾችን አስመልክተው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በአዋጁ ላይ በአስረጅ፣ በህዝብና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓት እንደሰበሰበ ገልጸዋል።
የንብረት ማስመለስ አዋጅ የመንግስትና የህዝብ ንብረትን ለማስመለስ የነበረውን የሕግ ክፍተት የሚሞላ እንደሆነ አስረድተዋል።
አዋጁ ዜጎች በላባቸውና በወዛቸው ንብረት እንዲያፈሩ የሚያበረታታ፣ በወንጀል ንብረት የሚያፈሩትን ተጠያቂ የሚያደርግ፣ የአገርን ዕድገት የሚያሳልጥ እንደሆነ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል።
ግለሰቦች በወንጀልና በሙስና ያፈሩትን ንብረት የሚያስመልስ በመሆኑ በተፈጻሚነቱ ላይ ጥንቃቄ ማድረግና አስፈጻሚ አካላትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እና የዜጎችን ንብረት የማፍራት መብት እንዳይጋፋ መታየት አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ በአዋጁ ሐብት የማፍራትና የማውረስ ሕገ-መንግስታዊ መብትን የሚቃረን ድንጋጌ አለመካተቱን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጸረ-ሙስና ትግል እንዲጠናከር የሚያደርግ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘና የተመዘበረ የአገር ሐብትን ለማስመለስ የሚያስችልና ሕገ-ወጥነትን የሚያስቆም አዋጅ እንደሆነም ጨምረዋል።
ምክር ቤቱ በአዋጁ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ ዝርዝር ውይይት በማድረግ በሦሰት ተቃውሞ እና በአራት ድምጸ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።