በትናንትናው ምሽት በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ተቆራርጦ ወደ ምድር ሲጓዝ የታየው ቁስ በሰው ሰራሽ የስፔስ ቁስ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦፓሻል ኢኒስቲትዩት ገለፀ፡፡
በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦፓሻል ኢኒስቲትዩት የከባቢ አየር ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ገመቹ ፋንታ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጊዜ ያበቃላቸው ሳተላይት እንዲሁም ሳተላይቶችን የመጠቁባቸው የሮኬት ቁርጥራጮች ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
በማንኛውም ሰው ሰራሽ መንገድ ህዋ ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ የመቃጠል እና ተሰባብሮ የመውረድ ምልክቶችን እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡
ክስተቱ የተፈጠረው በተፈጥሮአዊ የህዋ አካላት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
ከመሬት እና ከሶላር ሲስተም አፈጣጠር አንጻር አለቶች በመኖራቸው በማንኛውም ጊዜ እየተቆራረጡ ሊወርዱ እንደሚችሉ ነው ያነሱት፡፡
በዓለም ላይ እንደዚህ ያለ ሁነት እንደሚከሰቱ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ አልፎ አልፎ ቁጥራቸው በርከት ያሉት ወደ ምድር እንደሚወርዱም ገልፀዋል፡፡
ሰው የሚኖርበት ቦታ ከ 4 እስከ 5 በመቶ እንደማይበልጥ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ተቆራርጠው የሚወርዱ ነገሮች ከሰው ዕይታ ውጪ የሚከሰቱበት ሁኔታው ስለመኖሩም ጠቅሰዋል። አልፎ አልፎ ግን ለሰው ዕይታ እንደሚጋለጡም ነው አያይዘው የገለጹት፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓመት እስከ 6 ሺህ ድረስ ተቆራርጠው ምድር የሚደርሱ እና አለፍ ሲልም የአሸዋ ቅንጣት በመሆን ወደ ምድር የሚወርዱ ስለመኖራቸው ነው ተመራማሪው የተናገሩት፡፡
የሚቃጠሉበት ምክንያት ደግሞ ወደ ከባቢ አየር ሲገቡ ከከባቢ አየር ጋር በሚያደርጉት ፍትጊያ የሚፈጠር ስለመሆኑም አያይዘዋል፡፡
"አሁን እንዳለን መረጃ በደቡባዊ ክፍል የታየው ምስል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ነው የሄደው፤ አርፏል አላረፈም የሚለውን እስካሁን ማወቅ አልቻልንም" ብለዋል፡፡
ምድር ሦስት አራተኛዋ ውኃ በመሆኑ በአብዛኛው ውኃ ውስጥ እንደሚወድቅ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ካልወደቀ በስተቀር ጉዳት እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡