ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርና እና ምግብ ዋስትና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ከብራዚል የማህበራዊ እድገት፣ የቤተሰብ ድጋፍ እና የድህነት ቅነሳ ሚኒስትር ዌሊንግተን ዲያስ ጋር የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ፤የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት ግብርናን የማዘመን፣ የምግብ ሉዓላዊነት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በርካታ ስራዎች የተከናወኑ እና የተመዘገቡ ውጤቶችን በዝርዝር ገልጸዋል።
ዌሊንግተን ዲያስ በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተገኙ ውጤቶች ትምህርት የሚወሰደበት ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ብራዚል ድህነትን በመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸው፤በዚህ ረገድ በሚደረጉ ተግባራት በትብብር እና በቅርበት እንሰራለን ብለዋል።