የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ዜጎች አዳዲስና ዘመኑን የሚመጥኑ አገልግሎቶችን ፍለጋ ወደ ውጪ ሀገራት የሚደረጉትን ጉዞ የሚያስቀር መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ምክትል ሰብሳቢው ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ አዳዲስ የጤና አዋጆችን ማካተቱን ጠቅሰው፤ ይህም የጤና ተቋማት ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታን ያገናዘበ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ አገልግሎትን ፍለጋ ወደ ውጪ ሀገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን እና አላስፈላጊ ወጪዎችን እንደሚያስቀርም ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ የማሕበረሰቡን ባህልና እምነት የሚያከብር እንዲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥልቅ ውይይት እና ምክክር እንደተደረገበት ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በኢቢሲ የአዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" ቆይታቸው ተናግረዋል፡፡
የጸደቀው አዋጅ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
አዋጁ 12 ክፍሎች 60 አንቀጾች አካቶ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖርና ዘመኑን ያማከሉ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በአዋጁ መውለድ ያልቻሉ ባለትዳሮች የዘር ፍሬ በመውሰድ ልጅ እንዲያገኙ የሚያደርገው አሰራር መካተቱንም አንስተዋል፡፡
ይህ አዋጅ በጣም ብዙ ነገሮችን ይቀይራል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ ወቅቱ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ደህንነትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ያጎለብታል ብለዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ተስፋዬ ቦጋለ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ መከላከል ላይ ብቻ ያተኮረ ሲሆን አዲሱ አዋጅ ግን አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በርካታ የጤና ተቋማትም ይህን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለፁት፡፡
አስክሬንን ለምርምር መጠቀም እና የአይን ብሌን መለገስ የሚሉ ጉዳዮች በአዋጁ እንደሚገኝበትም አንስተዋል፡፡
ማንኛውም የጤና ማዕከላት የህክምና መሳሪያዎች ማሟላት እንደሚገባቸውም አዋጁ ይደነግጋል ብለዋል፡፡
የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡
በሜሮን ንብረት