በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በሚገኘው የከሰም ግድብ አከባቢ የሚኖሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦችን ሌላ አከባቢ ላይ የማስፈር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ በዞኑ የተቋቋመው ኮማንድፖስት ገለፀ።
የከሰም ግድብ የመሬት መንቀጥቀጡን እንዲቋቋም ታስቦ በትላልቅ አለቶች እና አሸዋ የተሰራ ግድብ በመሆኑ በሬክተር ስኬል እስከ 7 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋም ግድብ መሆኑን የከሰም ግድብ አስተዳደር ተወካይ እና የግንባታ አማካሪ መሃንዲስ ብንያም ውብሸት ተናግረዋል።
ግድቡ በ1997 የግንባታ ስራው ተጀምሮለት በ2012 አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት አቶ ብንያም ውብሸት፤ በመሬት መንቀጥቀጡ እስካሁን ግድቡ ላይ የደረሰ ምንም አይነት ስጋት አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
በግድቡ በታችኛው አከባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ወደ ሌላ አከባቢ እንዲሰፍሩ በማድረግ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በዞኑ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ አቶ አህመድ ኢብራሂም ገልፀዋል።
የከሰም ግድብ 500 ሚሊዮን ሜትሪክ ክዩብ ውሃ የሚይዝ ሲሆን 94 ሜትር ቁመት እንዳለው ተገልጿል።
በአጠቃላይ ግድቡ ከ20 ሺ ሄክተር በላይ እርሻ የማሰራስ አቅም ያለው ግድብ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
በሁሴን መሀመድ