የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ስኬታማነት ለማስቀጠል የታክስ መሰረቱን በማስፋት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የፌደራልና የክልል የፋይናንስ፣ የገቢዎች እና የፕላን መስሪያ ቤቶች የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በመድረኩ እንደገለፁት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራ ጠንካራ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች መካሄዳቸውንና የተለያዩ ድጎማዎችን ተከትሎ የመንግስት ወጪ ከፍ ማለቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባም ገልፀዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ስኬታማነት ለማስቀጠል የታክስ መሰረቱን በማስፋት በፌደራልም ሆነ በክልሎች ገቢ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ተብሏል።
በምክክር መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እንዲሁም የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በገንዘብ ሚንስቴር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ፣የክፍያ ሥርዓትና በጀትን በአግባቡ ለመጠቀም የጋራ አደረጃጀት እንደሚፈጥርም ይጠበቃል።