በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት የ5 ሰዎች ሕይወት አለፈ

13 Hrs Ago 131
በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት የ5 ሰዎች ሕይወት አለፈ
በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ግዛት ማክሰኞ እለት የተነሳው ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ሲሆን በአደጋው እስከ አሁን የ5 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡
 
ሰደድ እሳቱ ከ10 ሄክታር ተነስቶ በከተማዋ ባለው ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ምክንያት 80 ኪሎሜትር በሰዓት በፍጥነት በመጓዝ በከፍተኛ ሁኔታ መዛመቱ ተገልጿል።
 
በአደጋው ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሕንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸው ተነግሯል፡፡
 
ይህን ተከትሎ 200 ሺህ ነዋሪዎች የውኃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል ተብሏል፡፡
 
ሎስአንጀለስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የምትገኝ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባደን ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የፌደራል በጀት ማፅደቃቸውም ተጠቁሟል፡፡
 
በሎሳንጀለስ ዙሪያ የተቀሰቀሰው ከባድ የሰደድ እሳት አደጋ ትናንት ምሽት ጀምሮ ወደ ሆሊውድ ኮረብታዎች እየተስፋፋ መሆኑንም ቢቢሲ ዘግቧል።
 
አደጋውን ለመግታት በምድር እና በአየር እሳቱን የማጥፋት ስራ እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።
 
ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙ ሲሆን፣በዚህም ከአደጋው ስፍራ ወደ ሌላ ቦታ እያቀኑ በሚገኙ ነዋሪዎች ሳቢያ የትራፊክ መጨናነቅ መፈጠሩም ነው የተነገረው፡፡
 
አኩ ዌዘር የተባለው ተቋም በእሳት አደጋው የደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ከ 50 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት ገልጿል።
 
የሙቀት መጨመር፣ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች መስፋፋት እና መሰል የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ለአደጋው መከሰት ብሎም መባባስ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ነው የተገለፀው፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top