መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛውንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጀ እንሚወስድ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1.25 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን የገለፁት ሚንስትሩ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሸጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ አለው ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በኬንያ 1.351፣ በሩዋንዳ 1.136፣ በኡጋንዳ 1.299፣ በታንዛንያ 1.127፣ ማላዊ በ1.459፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብልክ 1.746 እንዲሁም በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባር ተጠምደዋል ነው ያሉት።
እነዚህ ባዳንዳዎች የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም፤ ራሳቸውን ለህዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለህዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉም ብለዋል።
ይህን የሚያደርጉት እውነታውን ስለማያውቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንዳይገለጥ ነው ያሉት ሚንስትሩ፤ ተሳስተው እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለው በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በህብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንደማያነሱ ገልፀዋል፡፡
ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጣራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን ስለሚጠይቅ ነው፤ እነሱ ይህ የላቸውም በማለት ድርጊታቸውን ኮንነዋል፡፡
“በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቻው አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጣል እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው፤ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነው፤ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግስት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም ነዉ፣” ነው ያሉት ሚኒስትሩ በፅሁፋቸው፡፡
“በነጻ ገበያ ውስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ሥርዓት መንግስት እንዲያደርግ የማይገደድባቸው ጉዳዮችን በማንሳት መንግስትን ይከሳሉ፡፡ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም” ብለዋል።
“መንግስት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል፤ በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል፤ ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የህብረሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ ይሠራል፤ ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ይረዳል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድሃኒትና መሰል የጤና ጉዳዮች በዓመት ከፍተኛ የሚባለውን ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽለ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው። የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ስራም ተጀምሯል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን መንግስት በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
“መንግስት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው፤እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል” በማለት በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አሳስበዋል።