ከለውጡ ወዲህ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ተሰርቷል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

3 Hrs Ago 38
ከለውጡ ወዲህ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ተሰርቷል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት፤ ተቋሙ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ የሠራዊት አደረጃጀት እና ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፣ ሠራዊቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጣ አካታች እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው መደረጉን ገልጸዋል።  

ከለውጡ በኋላ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ አለም እና እምነት ነጻ በማድረግ ሙያውን ብቻ መሰረት ያደረገ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ሰላም የሚጠብቅ ሆኖ እንዲቋቋምና ከዚህም የሚያፈነግጥ ሠራዊትና አመራር ካለ በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

የፖለተካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት በሚፈልጉ ኃይሎች የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተታለው እና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ተደልለው ጨካ ገብተው የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ በተደረገው ጥረት መልካም ውጤት እንደተገኘም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህንም ተጠቂዎች የመከላከያና ፖሊስ ተቋማት የሚያወጣቸው መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆነው ሲገኙ ተቋሞችን የሚቀላቀሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መስፈርቶችን የማያሟሉ ተጣቂዎችን መሳሪያቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ የመንግስት ኃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ እና በሀገሪቱ የተጀመሩ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ሀይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የሀገሪቱ መከታና ኩራት መሆኑን ገልፀዋል።

የሰላም አማራጭ መንገድን መከተል ሁልግዜም ቅድሚያ የሚሰጠውና የሀገርን ልማት ከዳር ለማድረስ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አባላቱ ጠቁመዋል፡፡

ይህንን አካሄድ በመጻረር የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ሽፍታዎች ላይ መከላከያ ሠራዊት ህግ የማስከበር እርምጃ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት ያለው መሆኑን መግለፃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top