የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ (ኃይል ሙሌት) ስርዓትን የተመለከተ መመሪያ ማጽደቁን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
መመሪያው በቤት ውስጥና ለንግድ ዓላማ የሚውሉ የኃይል መሙያ ስርዓት ቴክኒክና የኤሌክትሪከ የክፍያ ሥርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ነው ተብሏል፡፡
መመሪያው በዋናነት የፈቃድ መስፈርቶች፤ የቴክኒካል ስታንዳርድ፤ መሟላት የሚገባቸው የደህንነት መስፈርቶች እና የኤሌክትሪክ ክፍያ ተመን ማካተቱ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም መመሪያው የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት አቅራቢዎችን፣ ተጠቃሚውን፤ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅራቢዎችን እና የተሸከርካሪ ባለቤቶችን መብትና ግዴታ ያስቀምጣል ነው የተባለው፡፡
የኃይል መሙያ ሥርዓት አገልግሎትን በተመለከተ በቤት ውስጥ፣ ለህዘብ መገልገያ እና ለራስ አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ ሲስተሞች በሚል በሶስት ክፍል የተከፋፈለ ሆኖ መዘጋጀቱን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡
መመሪያው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በተመለከተ ከግሪድ ለሚቀርብም ሆነ ከግሪድ ውጪ ለሚቀርብ የሃይል አማራጮች ገዢ የሆነ ህግ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡
ፈቃድን በተመለከተ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ከሚውሉ በስተቀር ለራስ አገለግሎት እና ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ የኃይል መሙያ ከመገጠማቸው አስቀድሞ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ፈቃድ መውሰድ እንደሚገባ መመሪያው ማስቀመጡም ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ ባሻገር ለሃይል መሙያ ስርዓቱ የሚቀርብ ኤሌክትሪክን በተመለከተ ኤሌክትሪክ ከመገናኘቱ አስቀድሞ የብሔራዊ ግሪድ ኮድን ያከበረና በመመሪያው የተመለከቱ የቴክኒክና የደህንንት መስፈርቶች መሟላት እንደሚገባቸው ነው የተገለፀው፡፡
ከኤሌክትሪክ ታሪፍ ጋር በተገናኘም ከባለስልጣን መ/ቤቱ የሃይል አቅርቦትና ሽያጭ ፈቃድ የወሰዱ ተቋማት ለባለስልጣኑ የታሪፍ ፕሮፖዛላቸውን አቅርበው ሲያፀድቅ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ መመሪያው ያሳያል ተብሏል፡፡
የመሠረተ ልማት መገንቢያ ቦታዎችን በተመለከተ መመሪያው በየ50 ኪሎ ሜትር በፍጥነት መንገዶች ላይ በሁለቱም የመንገድ በኩል እንዲቋቋም በተጨማሪም ለከባድ ተሽከርካሪዎች እንደ አውቶቢስ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች በየ120 ኪሎ ሜትር ቢያንሰ አንድ የሃይል መሙያ እንዲኖር እንደሚፈቅድ ተገልጿል፡፡