ከብስራተ ወንጌል ሬዲዮ እስከ ኢቢሲ ድምጹን ለታሪክ ያስቀመጠ “ንጉሥ”
በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን እያዝናና ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው ማሕሙድ አሕመድ
60 ዓመታትን ሙዚቃ የተነፈሰ እንደብሔራዊ መዝሙር የሚዜም ሥራ የሰራ ታሪከኛ
********************
ሁሉም በትዝታ ንጉሥነቱ በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት፣ ሰብዓዊነትን ከሙያ ያጣመረው፣ ሕይወትን ለማሸነፍ ከጉልበት ሠራተኝነት እና ሊስትሮነት እስከ ወጥ ቤት ሠራተኝነት ሥራ ሳይመርጥ ሁሉንም የሠራ፣ ቤተሰቡን ለመርዳት የወጥ ቤት ሠራተኛ ሆኖ ሲሠራ ከነበረበት ተነሥቶ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ማማው ላይ የደረሰ እና ብዙ የሚነገርለት ታሪክ ያለው ድምፀ መረዋ ነው።
በ1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ መርካቶ አሜሪካ ግቢ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የተወለደው አርቲስት ማሕሙድ አሪዞና የምሽት ክበብን ድልድይ አድርጎ በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ ዘመን የማይሽራቸውን ሙዚቃዎች ለአድማጭ ማቅረብ ጀመረ።
ጥላሁን ገሠሠ (የክብር ዶክተር) ከምድር ጦር ኦርኬስትራ አባላት ጋር በ1968 “አይከዳሽም ልቤ”ን እና “የኔ ማስታወሻ”ን ሲያቀርብ ደቀመዝሙሩ ማሕሙድም በለማ ደምሰው አቀናባሪነት በምድር ጦር ኦርኬስትራ አጃቢነት “አልማዝ ዕንቁ መሳይ”፣ “ችላ አትበይ”፣ “ዓለም ዓለም" እና “እንዴት ልለፈው” የተባሉትን ዜማዎች በፊሊፕስ ሙዚቃ ቤት አሳታሚነት በተመሳሳይ ዓመት ለአድማጭ አድርሷል።
በትዝታ ቅኝት አጨዋወቱ “የትዝታው ንጉሥ” የሚል ቅጽል ስም ከሕዝብ የተሸለመው
የያኔው አፍለኛ ወጣት ዳግም ልደቱ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ይሁን እንጂ የሙዚቃ መነሻ ቦታው ግን መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኘው ኦሪዞና የምሽት ክበብ ነበር ፤ ጊዜውም በ1954 ዓ.ም ነው።
“አንድ ግብጻዊ ጎረቤት ነበረን” የሚለው ማሕሙድ፣ “ይህ ሰው ከሾፌሮች ሆቴል ባለቤት ጋር በመሆን የምሽት የሙዚቃ ክበብ ለመከፈት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ስሰማ በእናቴ አማላጅነት እዚያ ተቀጠርኩ” ይላል። የጉልበት ሠራተኛ በመሆን በመገንባት ላይ ያለውን የአሪዞና ክበብ የተቀላቀለው የጥላሁን ደቀመዝሙር በጊዜው ከአናፂዎች ጋር አናፂ፤ ከቀለም ቀቢዎች ጋር ቀለም ቀቢ እየሆነ በሚያገኘው ገንዘብ ቤተሰቦቹን ይረዳ ጀመር።
በ1954 የቤቱ ጥገና ተጠናቆ የአሪዞና የምሽት ክበብ በይፋ ተከፈተ። ማሕሙድም ከጉልበት ሠራተኝነት ወደ ወጥቤት ረዳትነት ተዛወረ። የአሪዞና የምሽት ክበብ ባለቤት አቶ ካሣሁን ገብሩ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባላትን በተሻለ ክፍያ በቤቱ ሲያሠራም ማሕሙድ ከምግብ ማብሰያ ከፍል እየወጣ የደረሰውን ምግብ ለእነርሱ የማቅረብ ኃላፊነት ተጣለበት። በዚህ ወቅት ነበር ጥላሁን ገሠሠ፣ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ ተፈራ ካሣ እና እሳቱ ተሰማን የመተዋወቅ ዕድል ያገኘው።
ጀምበር ስታዘቀዝቅ የደስታ መናኸሪያ የሚሆነው አሪዞና አንድ ምሽት ግን ፀጥታ አረበበበት። የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባላትን ለመመልከት የመጡት ታዳሚዎች በእነ ጥላሁን ገሠሠ ለሥራ ወደ ድሬዳዋ መሄድ የሚወዷቸውን ድምፃዊያን ለማየት አልቻሉም። እናም "ገንዘብ ከፍለን የገባነው እኮ እነ ጥላሁን አሉ ብለን ነው” የሚል ንትርክ ማንሣት ጀመሩ። ነገሩ እየተካረረ በመሔዱም ታዳሚዎቹ “የከፈልነውን ብር መልሱ” ማለት ጀመሩ።
የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾቹ ግን የተፈራ ካሣን "አልጠላሽም ከቶ” የተባለ ዜማ በመሣሪያ ብቻ ማቅረባቸውን አላቋረጡም። ማሕሙድ በዚህ መሃል ከወጥ ቤት ወጥቶ የባንዱን አባላት ይሄን ሙዚቃ እኔ ልጫወተው አላቸው። ከባዶ ይሻላል ያሉ የመሰሉት የሙዚቃ ቡድኑ አባላትም ፈቀዱለት። በአሪዞና ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ “ጊዜ ቢያሳየኝም ጥፋትሽን አጉልቶ፤ እኔ እንዳንች አልሆንም አልጠላሽም ከቶ” የተሰኙትን ስንኞች ከፍርሃት ጋር ያንጎራጎረው ማሕሙድ አሕመድ በተደጋጋሚ “ቢስ” የሚባልለት ተአምረኛ ድምፃዊ ለመሆን በቃ። የተዘራ ኃይለሚካኤልን “ይህም አለ ለካ˝ በእዚያው መድረክ ላይ የቀጠለው የድንገቴው ድምፃዊ የዋዛ የመሰለ ሙከራው ወደ ዕውቅና ሰገነት የሚያወጣ መሰላል እና የቀጣይ ሕይወቱ ጎዳና ጥርጊያ ሆነለት። የአሪዞና ከበብ ባለቤትም በጭንቅ ሰዓት የደረሰላቸውን ማሕሙድ ለመካስ በማግስቱ ሙሉ ልብስ ገዝተው አበረከቱለት።
ከቀናት በኋላ ከድሬዳዋ የተመለሱት እነ ጥላሁን በመደበኛ ሥራቸው ላይ ለመገኘት ወደ ኦሪዞና ክበብ ሲያመሩ ምግብ አቅራቢያቸውን ማሕሙድን ከመድረክ ተሰይሞ አገኙት። በአጨዋወቱ ተገርመውም የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ግጥሞች የያዘ ደብተር ሰጥተውት ከእነርሱ ጋር እያጠና እንዲያቀርብ ተባበሩት። ማሕሙድ በአሪዞና የምሽት ክበብ ላይ ስሙ እየገነነ ቢመጣም የእቴጌ መነን ሞት ግን የአዲስ አበባን የምሽት ክበቦች ከዳር እስከዳር እንዲዘጉ ያደረገ አጋጣሚን ፈጠረ። ይህ መነሻ ሆኖም ማሕሙድ ካለመድረክ ለተወሰኑ ወራት ቆየ። ከሁለት ወራት በኋላ ብሔራዊ ሐዘኑ ሲያበቃም ማሕሙድ ዳግም በአሪዞና የምሽት ከበብ መድመቁን ቀጠለ።
በወርኀ ታኅሣሥ 1955 ለፊደል ሠራዊት የገቢ ማሰባሰቢያ ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅት ተደግሷል። ሁሉም ወታደራዊ የሙዚቃ ክፍሎች በሚሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ አንድ ግለሰብ ባልተለመደ ሁኔታ በሕዝብ ፊት ሊፈተን እና የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራን መቀላቀል አለመቀላቀሉን ሊወሰን ከመድረኩ ጀርባ ተቀምጧል። ትንቢተኛው መድረክ መሪ መቶ አለቃ ገዛኸኝ ደስታ ለተመልካቹ እንዲህ ሲል ተናገረ። "አንድ አዲስ ልጅ ዛሬ እናቀርብላችኋለን፤ ልጁ ምናልባት የጥላሁን ገሠሠ ደቀ መዝሙር ይሆናል ብለን እንገምታለን፤ ይሁን ካላችሁ ይቀጥላል” ብለው ለሕዝቡ አሳወቁ። ታዳሚውም ይሁንታውን ገለጸ። በሕዝብ ፊት ሊፈተን ከመድረኩ የተገኘው ትንሹ ልጅ ሙዚቃውን ማሰማት ጀመረ።
“ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም፣
ግን እስካሁን ድረስ አላወቀሽልኝም፣
ሰላምን ለማገኘት አጥብቄ ብመኝም፣
ታበሳጭኛለሽ አላወቅሽልኝም። " በማለት አዜመ።
ማሕሙድ የራሱ የሆነችውን የመጀመሪያ ዜማውን ማሰማቱን ቀጥሏል። በመድረኩ የታደሙት ሁሉ ለወጣቱ ማሕሙድ አድናቆታቸውን ለገሱ። ማሕሙድ ገና ከመድረክ ሳይወርድ በሕዝቡ አቀባበል ብቻ ፈተናውን አንዳለፈ ገብቶታል። ከመድረክ ወርዶ ወደ መልበሻ ክፍሉ ሲያመራ “በሕዝብ ፊት ተፈትነህ ካለፍክ ትቀጠራለህ" ያሉትን ሻለቃ ግርማ ሀደጎ ተመለከታቸው። በደስታ ፊታቸው የተዋጠው ሻለቃ ለማሕሙድ የመድረክ ብቃቱን ሳይሆን የቅጥሩን ሁኔታ የተመለከተ ምክር ብቻ ሰጡት። ሻለቃ ለቀጣሪዎቹ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አመራሮች በሲቪልነት ካልሆነ በወታደርነት አልቀጠርም እንዲላቸውም መከሩት።
ማሕሙድ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሰዎች እንደወደዱት ስለተረዳ ሻለቃ ሀደጎ እንዳሉት በሲቪልነት መቀጠር እንደሚፈልግ ነገራቸው። የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አመራሮች ተስፈኛውን ወጣት ከመቅጠር ውጭ አማራጭ ስላልነበራቸው በ60 ብር ደሞዝ ማሕሙድ አሕመድን ታኅሣሥ 15 ቀን 1955 ቀጠሩት።
የፖሊስ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ‘ትምህርት ከሌለህ አንቀጥርህም’ ያለው ማሕሙድ የምድር ጦር ኦርኬስትራ ‘መጀመሪያ ወታደር ሆነህ አገልግል’ ያለው ቀጣዩ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ኮከብ በአገሪቱ ትልቁ ኦርኬስትራ ፈልጎ ብቻ ሳይሆን ተፈልጎ ቅጥሩ ተፈጸመ።
የትዝታው ንጉሥ ለ11 ዓመታት ያህል የዘለቀበትን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ በ1966 ዓ.ም ተሰናበተ። ለዚህ መነሻው ደግሞ ኦርኬስትራው ይከፍለው የነበረው 250 ብር ደሞዝ ለእርሱ እና ለቤተሰቦቹ በቂ አለመሆኑ ነበር። በዚህ መነሻም ወደ ራስ ሆቴል አቅንቶ አይቤክስ ባንድን ተቀላቀለ። አይቤክስ በማሕሙድ አሕመድ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥም አዲስ ነገርን ለማስተዋውቅ የጣረ ባንድ ነበረ።
ማሕሙድ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ያደረገው ውህደት ለኢትዮጵያ የሀገረሰብ ሙዚቃዎች አዲስ ገጸ በረከትን ይዞ ስለመምጣቱ የዳዲሞስ ባንድ ሊድ ጊታር ተጫዋች እና የሙዚቃ ታሪከ አዋቂው ብሩክ አስገዶም ይናገራል። ብሩክ እንደሚለው፣ “እስከ 1968 የነበረው የሙዚቃችን መንገድ ባህላዊ ዜማዎችን ለባሕል ድምፃዊያን ብቻ የተወ ነበር፤ ማሕሙድ አሕመድ ከአይቤክስ ባንድ ጋር የሠራቸው ሙዚቃዎች ግን ይህን ታሪክ ሽረውታል”።
እነዚህ ዜማዎች አስቀድመው በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ቀረጻቸው የተካሄደ ሲሆን፣ በኋላም ጥራታቸው ተጨምሮ በፍራንሲስ ፋልሴቶ አማካኝነት በተሰበሰቡ የኢትዮጲክስ የሙዚቃ ስብስብ ቁጥር ሰባት ላይ ተካትተው ለገበያ ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ በሸፍረዲን ሙሳ ግጥማቸው የተጻፈው “ዓባይ ማዶ አና እንቧ በለው” ተጠቃሽ ናቸው። በኢትዮጲክስ ቁጥር 6 ላይ የሚገኙት “አልማዝ ምን እዳ ነው፣ ኩሉን ማን ኳለሽ" እና "አሻ ገዳዎ” ከላይ በብሩክ ለተነሣው ሐሳብ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ናቸው።
ማሕሙድ አዲስ መንገድን አበጅቶባቸዋል የሚባሉት ከላይ የተጠቀሱ ሙዚቃዎች በአንዳንዶች አገላለጽ የእርሱን ታላቅነት ያሳዩ ሲሆኑ በሌሎች ምልከታ ግን ለማሕሙድ የማይመጥኑ የተለመዱ የባሕል ጨዋታዎች ተደርገው ተቆጥረዋል። ማሕሙድ ራሱ እንደሚገልጸውም “አልማዝ ምን እዳ ነው" የሚለው ዜማ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ለመወደድ ቢችልም አንዳንድ ሰዎች ግን ‘ፍራሽ አዳሽ’ እያሉ ሙዚቃዎቹን እንዳጣጣሏቸው ያስታውሳል።
አይቤክስ ባንድ በትዝታው ንጉሥ ሙዚቃዎች በደመቀበት 1960ዎቹ መገባደጃ ላይ በርከት ያሉ ዜማዎችን ያሳተመው ከሊፋ ሪከርድስ የተባለው አሳታሚ ድርጅት ነው። እነዚህ በሸዋሉል መንግሥቱ እና ሸረፈዲን ሙሳ ለማሕሙድ የተሰጡ ሙዚቃዎችም "ኧረ መላ መላ"፣ "መቼ ነው”፣ “አታውሩልኝ ሌላ"፣ "አሆሆ ገዳማይ"፣ " ስደተኛ ነኝ፣ "ሳምራዬ"፣ "እንዴት ነሽ ገዳም” እና “አሸወይና” የተሰኙ መዚቃዎች ሲሆኑ “እባክሽ ታረቂኝ” የተባለውን ዜማም በዚሁ ወቅት የተሠራ ነበር።
ማሕሙድ በዚህ ዘመን ከአይቤክስ ባንድ ባለፈ ከቬነስ ባንድ ጋር በመጣመርም ሙዚቃዎችን ለአድማጭ አድርሷል። ለዚህ አብነት የሚሆኑትም “ናፍቆት ነው የጎዳኝ” እና “ያስደስታል” የተባሉት ሥራዎቹ ናቸው። ናፍቆት ነው የጎዳኝ የተባለውን ሙዚቃ የደረሰው የአፋን ኦሮሞ ዘመናዊ ሙዚቃ ንጉሡ ዓሊ ቢራ ነበረ። እነዚህን ሙዚቃዎች ግርማ በየነ ሲያቀናብር አምኃ እሸቴ ደግሞ የአሳታሚነቱን ሚና ተወጥቷል። በዕድገት በኅብረት ዘመቻ ሰሞን “አታውሩልኝ ሌላ”ን የተጫወተው ማሕሙድ ይህ ሙዚቃ በተለያዩ ወገኖች ጥርስ እንዳስነከሰበት ይናገራል።
በከብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ቆይታው ባስቀረጻቸው "መላ ትስጠኝ"፣ "ትዝታ"፣ “ሁሉም በጊዜው ነው”፣ “ፍቅር በዛብኝ”፤ “የሺ ሐረጊቱ” እና "እነማን ነበሩ" በመሰሉ ሸክላዎች ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ማሕሙድ፣ ከእነዚህ ሥራዎቹ ጀርባ የነበሩትን ሰዎች ሁሌም ያደንቃል። “እነማን ነበሩ”ን ታዋቂው የክብር ዘበኛ ሰው ሠይፉ ኃይለማርያም ያቀናበረው ሲሆን “የሺ ሐረጊቱ”ም በፍቅሩ ወልደሥላሴ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የተሠራ ሙዚቃ መሆኑ በጊዜው ተዘግቧል። “መላ ትስጠኝ” በመጀመሪያ በአየለ ማሞ የተዜመ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በማሕሙድ ሲቀርብ ኃይሉ ወልደማርያም በቅንብሩ በኩል ተሳትፈውበታል።
ኃይሉ ከዚህ ሥራ በተጨማሪም በፊሊፕስ በኩል ለገበያ በቀረበው “ትዝታ” ዜማ ላይ በቅንብሩ በኩል ስማቸው ተጠቅሶ እናገኛለን። “ፍቅር በዘበዘኝ” የተባለው የማሕሙድ አሕመድ ሙዚቃ በክፍሉ አባል እና ድምፃዊ እንዲሁም የዜማ እና ግጥም ደራሲ በሆኑት ሸዋንዳኝ ወልደየስ ግጥሙ የተጻፈ ሲሆን፣ “ሁሉም በጊዜው” በተባለው ዜማ ግጥም ድርሰት ላይ የቴአትር ከፍል አባል የነበሩት ዘውገ ገብረ መድኅን እና አየለ ማሞ ተሳትፈዋል።
ማሕሙድ አምኃ ያሳተማቸውን “ጊዜ ደጉ ነገር” እና “ይቅር መመካትሸ” የተባሉትን ሙዚቃዎች በዘ-ኤኮየተርስ አጃቢነት በማቅረብ በባንዱ የነገሰ ሲሆን፣ የሸክላ ሕትመት ዘመን ማክተምን ተከትሎም በ1972 ዓ.ም በካሴት ሥራው ብቅ ብሏል። ከዚህ በኋላም ዳህላክ እና ሮሐን ከመሰሉ ባንዶች ጋር በመጣመር በርካታ አልበሞችን ለአድማጭ አድርሷል።
በዓመታዊው “የቢቢሲ ሬዲዮ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ሰው” ሽልማት አሸናፊ የሆነው የትዝታው ንጉሥ ማሕሙድ አሕመድ፣ ከሌሎች በተለየ መልኩ ከሀገሪቱ ታዋቂ ድምፃዊያን ሳይቀር የግጥም ድርሰት በገፍ ሲቀርብለት የኖር የሙዚቃ ሰው ነው።
ፍሬው ኃይሉ "አልማዝ አልማዝዬ" የተባለውን መዚቃ ሲያቀርብለት ምኒልክ ወስናቸው “የፍቅር ወጥመድ ነው" በተባለው ሥራው ላይ ተሳትፎ አድርጓል። የምድር ጦሩ የሙዚቃ ሰው ኮሎኔል ለማ ደምሰውም “እንቁ መሣይ”፣ “ዓለም ዓለም”፣ “እንዴት ልለፈው” እና “ችላ አትበይ" የተባሉትን ሙዚቃዎች ለማሕሙድ በመስጠት ስሙን አጽፏል።
የቤተሰቡን ሕይወት ለመለወጥ ከጉሊት ነጋዴነት እስከ ወጥቤት ሠራተኝነት የዘለቀው ማሕሙድ አሕመድ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር ከተዋወቀ በኋላም የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረክ በማስተዋወቅ በኩል አርማ ሆኖ አገልግሏል።
ስድስት አስርት አመታትን የዘለቀው የትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህመድ የመጨረሻ ኮንሰርት ቅዳሜ ጥር 3 በሚሊኒየም አዳራሽ በታላቅ ድምቀት ይካሄዳል።
የዚህ ታሪካዊ ኮንሰርት ብቸኛ የሚዲያ አጋር ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይህን ታሪካዊ ኮንሰርት ከተካሄደ
በኋላ በላቀ የፕሮዳክሽን ጥራት በኢቲቪ መዝናኛ ያቀርባል።
የትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህመድ ሥራዎች በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ተቀርጸው ለዚህ ትውልድ እንደደረሱ ሁሉ አሁን ደግሞ ለታሪክም ለትውልድም የሚተላለፈው የመጨረሻ ኮንሰርት በኢቢሲ ይቀመጣል።
በለሚ ታደሰ