የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሀገር አሜሪካ ከሰሞኑ እሳት እና በረዶ ለጥፋት አብረውባት ሰንብታለች፡፡
ሀገሪቱ በአንድ በኩል ያገኘውን ሁሉ በሚበላ ከባድ ሰደድ እሳት፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጥንትን በሚሰረስር በረዶ ተፈትናለች፡፡
በሎስ አንጀለስ ከተማ የተነሳው ሰደድ እሳቱ እስካሁን የ10 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከ170 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችም መኖሪያቸውን ለቀው ለመሸሽ በተጠንቀቅ እንዲያሳልፉ አድርጎ ነበር፡፡
በከባድ ሙቀት እና ኃይለኛ ንፋስ የታጀበው ሰደድ እሳቱ ከ10 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን፣ ህንጻዎችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡
ስመ ጥር የአሜሪካ የፊልም ባለሙያዎች መኖሪያ እና የግዙፉ የሆሊውድ የፊልም መንደር መገኛ የሆነችው ከተማዋ በእሳት እና ጭስ ጽልመት ለብሳ አሳልፋለች፡፡
በሌላ በኩል ከሰሞኑ 7 የሚደርሱ የሀገሪቱ ግዛቶች ከባድ በረዶ ወርዶባቸው ቅዝቃዜ ሲቆረጥማቸው ሰንብቷል፡፡
በበረዶ ውሽንፍሩ የ5 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያ፣ ካንሳስ፣ ሚዙሪ፣ ኬንታኪ፣ አርካንሳስ እና ሌሎች ግዛቶችም የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጀው ነበር፡፡
የበረዶ ውሽንፍሩ በሀገሪቱ ከ2 ሺህ 300 በላይ በረራዎች እንዲሰረዙ፣ 9 ሺህ በረራዎችም እንዲዘገዩ እንዲሁም 190 ሺህ የሚደርሱ ቤቶች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጩ እንዲሆኑም ምክንያት ነበር፡፡
ሀገሪቱን ያስጨነቀው የበረዶ ውሽንፍሩ እስከ 8 ኢንች ድረስ ወደ ላይ ሊወጣ እንደሚችል እና ደቡብ ምስራቅ ኦክላሆማን ይዞ እስከ ካሮላይና ግዛት ሊዘልቅ እንደሚልችልም የሀገሪቱን ብሔራዊ የአየር ትንበያን ጠቅሶ ዩኤስኤ ቱደይ ዘግቧል፡፡
በመሐመድ ፊጣሞ