የካፒታል ገበያ አሠራር በኢትዮጵያ መጀመር ፈጠራን እና ኢንቨስትመንት የሚያበረታታ እንዲሁም የተማከለ ሥርዓት ያለው የካፒታል ገበያ መፍጠር እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" ላይ የቀረቡት የካፒታል ገበያ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ኃላፊዎች በዚህ የግብይት ሥርዓት የኩባንያ ባለቤቶች ለግለሰቦች ድርሻ በመሸጥ ገንዘብ እንዲያሰባስቡ ከዚህም ድርሻም በተጨማሪ የብድር ሰነዶችም እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልኩ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መጀመር ኢንቨስተሮች ባላቸው ፍላጎት እና መስፈርት መሰረት በራሳቸው መገበያያት የሚያስችላቸውን የተሟላ ህጋዊ ማዕቀፍን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ መገንባት የምታስበው የካፒታል ገበያ ያለ ቴክኖሎጂ ሚታሰብ ነገር አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም በግብይት ሂደት የሚኖሩ ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ሰውአለ አባተ በበኩላቸው፤ ካፒታል የሚፈልጉ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት እና ፕሮጀክቶች በዚህ ገበያ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡
በኢንቨስተሮች እሳቤ የሚራመዱ ተቋማት ከዚህ በፊት አልነበሩም የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ገበያውን የሚቆጣጠረውም ሆነ ፍቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የአክሲዮኖችንም ሆነ ቦንዶችን ማሻሻጥ ላይ የተሰማሩ አካላት ሥራውን የሚሠሩት ራሱን የቻለ የብቃት ማረጋገጫ እና ፍቃድ ከኢትዮጵያ ካቢታል ገበያ ባለሥልጣን ሲያገኙ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡
በዚህ መንገድ ህጋዊ መንገዱን እና ሥርዓትን ተከትሎ መሄድ ከዚህ ቀደም ይፈጠሩ የነበሩ መጭበርበሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ሥርዓትን መስመር ማስያዝ ቀደም ብሎ መጀመሩን የሚያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) ሲሆኑ፤ አዋጁን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የመሰረተ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓለም ላይ ትላልቅ ኩባንያዎች የቢዝነስ ህልውናቸውን ያደረጉበት የካቢታል ገበያ 118 ትሪሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኒውዮርክ፣ ለንደን፣ ሻንጋይ እና ቶኪዮ በአፍሪካ ደግሞ ጆሀንስበርግ እና ናይሮቢ የካፒታል ገበያ ማዕከላት ናቸው ብለዋል፡፡
ባደጉት ሀገራት በስፋት የሚታወቀው እና በኢትዮጵያ ቢተገበር በሀገሪቱ የፋይናስ ሥርዓት ትልቅ ለውጥ ያመጣል የተባለውን የካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው በ2013 ዓ.ም የወጣው የካፒታል ገበያ አዋጅ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
አንድ የተማከለ የኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋይ ሰነድ እንዲኖር በማስቻል ቁጠባውን ኢንቨስት ማድረግ እንደሚቻል ነው ኃላፊዎቹ ያመላከቱት፡፡
ባንኮች ችግር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ለመንግሥት እና ለግሉ ዘርፍ ብቸኛ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆን የታመነበት ይህ የአክሲዮን ገበያ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች ከሚፈልጉት ኢንቨስትመንት አማራጭ ጋር ለማገናኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተነግሯል፡፡
በሜሮን ንብረት