ባለፉት ሥድስት ዓመታት የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ማቃለል ተችሏል፡-ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

13 Hrs Ago 72
ባለፉት ሥድስት ዓመታት የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ማቃለል ተችሏል፡-ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)
ባለፉት ሥድስት ዓመታት ምንም ዓይነት የንግድ ብድር ባለመፈጸም፣ ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ በማድረግና፣ ብድርን በከፍተኛ ሁኔታ በመክፈል የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ማቃለል መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
 
በዚህም ኢትዮጵያ አሁን ያለባት የዕዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ 13 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት። ከለውጡ በፊት ከ30 በመቶ በላይ እንደነበር በማውሳት።
 
ሚኒስትሯ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶችና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
መንግሥት የተከተለው አዲስ የኢኮኖሚና ማህበራዊ የፖሊሲ ዕይታ ብዝኃ ዘርፍን ያማከለ፣ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ያደረገና አካታች ስርዓትን ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ እኩል የእድገት ምንጭ እንዲሆኑ ትኩረት መሰጠቱንና የኢኮኖሚ ተዋንያን ሚዛን መጓደል እንዲስተካከል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
 
በዚህም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ይዞት የቆየውን ጉልህ ሚና ወደ ግሉ ዘርፍ የማሸጋገር ሥራ መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
 
በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተተገበረው ፖሊሲ ኢኮኖሚውን ማዘመንና ለውድድር ክፍት ማድረግ ላይ መጠነ ሰፊ ሪፎርም መደረጉን ነው ያነሱት።
 
ለዚህም የንግድ ህጉንና የኢንቨስትመንት አዋጁን ጨምሮ ከ80 በላይ ህግጋት መቀየራቸውን ተናግረዋል።
 
ይህን ተከትሎ የአገልግሎት፣ የንግድና ኢንቨስትመንትን ምህዳርን ያሻሻሉና ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
 
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመንግሥት ገቢን ከማሳደግ፣ የወጪ አስተዳደርን ከማስተካከል፣በጥናት ላይ የተመሰረተ የፕሮጀክት ትግበራና አፈጻጸምን ከማሻሻል፣ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ከማሸጋገር አንጻር አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
 
ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ልማት ፋይናንስ የተደረገበት መንገድ ሀገር በዕዳ ቀንበር እንድትማቅቅ ያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህንን ለማስተካከል በርካታ ሥራዎች በመከናወናቸው የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ማቃለል ተችሏል ብለዋል።
 
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ለአብነትም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር፣ ገቢ፣ የወርቅና የቡና የውጭ ገበያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።
 
አሁን ላይ ባንኮች ከሚሸጡት የውጭ ምንዛሬ ይልቅ የሚገዙት ከፍተኛ ብልጫ ማሳየቱንም ተናግረዋል።
 
የብሔራዊ ተቀማጭ መጠን በ200 በመቶ ማደጉን ገልጸው፤የኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ መፈታቱንም ነው ያነሱት።
ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግሥት ለደመወዝ፣ ለነዳጅ፣ ለመድሃኒት፣ ለሴፍትኔትና ሌሎች ድጎማዎች ከ400 ቢሊዮን ያላነሰ በጀት መመደቡን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
መንግሥት የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ቢያስቀጥልም በቅርቡ የዓለም የነዳጅ ዋጋንና የውጭ ምንዛሬ ለውጡን መሰረት በማድረግ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉን ጠቁመዋል። አሁንም ነዳጅ በኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ከ20 እስከ 26 ብር ቅናሽ እየተሸጠ ነው ብለዋል።
 
መንግሥት ድሃ ተኮር ፖሊሲ የሚከተል በመሆኑ ድጎማዎቹን ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የነዳጅ ግብይት ስርዓትን ዲጅታላይዝ ማድረግ፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠርና ነዳጅ በአግባቡ ለተጠቃሚዎቹ መድረሱን ማረጋገጥ ላይ አዳዲስ አሰራሮች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል።
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top