"እስከ መውለጃ ሰዓቴ ድረስ ልጄ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተነግሮኝ ነበር"፡- የሕክምና ስህተት ተጎጂ እናት

3 Hrs Ago 53
"እስከ መውለጃ ሰዓቴ ድረስ ልጄ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተነግሮኝ ነበር"፡- የሕክምና ስህተት ተጎጂ እናት
ሦስተኛ ልጄን ስወልድ ባጋጠመኝ የሕክምና ስህተት እኔ እና ቤተሰቦቼ የሥነ-ልቦና ጫና ደርሶብናል ስትል በሕክምና ስህተት ልጇ የተጎዳችባት እናት ወ/ሮ ሶስና ይርጋ ትናገራለች፡፡
 
ጤናማ የሆነ የእርግዝና ጊዜ አሳልፋ እንደነበር የምትገልፀው ወ/ሮ ሶስና፤ ልትወልድ 72 ሰዓት ሲቀር በልጇ አንገት ላይ እትብት መጠምጠሙን እና የከፋ ጉዳት እንደማያደርስ ከሕክምና ባለሙያዎች እንደተነገራት ታስረዳለች፡፡
 
"ከወሊድ በኋላም ነገሮች ልክ መሆናቸው ስለተነገረን ወደ ቤት አመራን" የምትለው ወላጅ እናት፣ ከቀናት በኋላ ግን ልጇ ላይ ለየት ያሉ ባህሪዎችን ማስተዋል መጀመሯን ትገልጻለች፡፡
 
ይህንንም ተከትሎ ወደ ጤና ተቋም ያመራችው እናት፣ በመውለጃዋ ወቅት ልጇ አንገት ላይ ተጠምጥሞ የነበረው እትብት የልጇ ጭንቅላት ላይ ጉዳት ማድረሱን ከሕክምና ባለሞያዎች እንደተነገራት በመግለጽ የገጠማትን የሕክምና ስህተት ታስረዳለች፡፡
 
ችግሩ በጊዜው ስላልተነገረኝ እና ልጄ አስፈላጊው የሕክምና እገዛ በወቅቱ ስላልተደረገላት በአዕምሮዋ ላይ በደረሰው ችግር ምክንያት መንቀሳቀስ እና እኩዮቿ የሚያደርጉትን መፈጸም እንዳትችል ሆናለች ስትል ነው ወ/ሮ ሶስና የምትገልጸው።
 
ልጇን በማሳደግ ሂደት ውስጥ እያሳለፈች ስላለው ከባድ ጊዜ እና የሥነ-ልቦና ጫና በመግለጽ፤ የሕክምና ስህተት በሚፈፅሙ የጤና ባለሙያዎች ላይ አስተማሪ እና ጠንካራ የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቃለች፡፡
 
የኢቲቪ አዲስ ቀን ፕሮግራም በ‘የሀገር ጉዳይ’ መሰናዶው የሕክምና ስህተትን እና ተጠያቂነቱን ተመልክቶታል፡፡
 
በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ጳውሎስ ተሰማ፤ የሕክምና ስህተት በእውቀት ማነስ ወይም በቸልተኝነት ሊፈጠር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡
 
በኢትዮጵያ ስህተቱን የሚፈፅሙ ባለሙያዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተፈጸመውን ስህተቱን የሚያረጋግጡ ገለልተኛ ተቋማት አለመኖራቸውን ያነሳሉ፡፡
 
ይህም ጥፋተኞችን ተጠያቂ በማድረግ አስተማሪ እና የማያዳግም እርምጃ እንዳይወሰድ እክል መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
 
የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የሕክምና ስህተት በቴክኖሎጂ እና የዘመነ የአሰራር ሥርዓትን ባልተገበሩ ሀገራት ላይ ትልቅ ችግር መሆኑን ያነሳሉ።
 
የሕክምና ባለሙያዎች ለሞያ መርሃቸው የሚገዙ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሊሆኑ ይገባል የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለሙያዎች ብቃታቸውን ከጊዜው ጋር ማሳደግ እንደሚገባቸው ይገልጻሉ።
 
ከሕክምና ስህተት ተጠያቂነት ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከፌደራል ባሻገር በክልሎችም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አስቀምጠዋል፡፡
 
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሕክምና ስህተት ጋር በተያያዘ የጀመረውን ከአገልግሎት ማገድ እስከ ሕጋዊ እርምጃ ያሉ ውሳኔዎችን ከፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ በተደረጉ ጥናቶች ለታካሚዎች ከሚታዘዙ 100 መድኃኒቶች ውስጥ 48ቱ ከበሽታው ጋር ተያያዥነት የሌላቸው እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
በአማካኝ በ1 ሺህ ቀናት ውስጥ 433 የሚሆኑ የሕክምና ስህተቶች እንደሚከሰቱ ተገልጿል፡፡
 
በሀገሪቱ ከሚደረጉ የቀዶ ጥገናዎች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት የሕክምና ስህተት እንደሚገጥማቸውም ነው የተመላከተው፡፡
 
ለዚህም ዋና ምክንያቶች የሕክምና ባለሙያዎች እና የታካሚ ቁጥር ያለመመጣጠን የሚፈጥረው ጫና፣ የሕክምና ግብዓቶች ያለመሟላት፣ የሕክምና የአሰራር ሥርዓቶችን ያለመጠበቅ፣ ለሕክምና ባለሙያዎች ወቅታዊ የሆነ ስልጠና ያለመስጠት እና የባለሙያዎች ቸልተኝነት እና መሰል ተግባራት መሆናቸው በዝርዝር ይቀመጣል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top