በጎንደር የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ስፍራ የእድሳት ስራ መጠናቀቁን የከተማው ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ

2 Hrs Ago 38
በጎንደር የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ስፍራ የእድሳት ስራ መጠናቀቁን የከተማው ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ
በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቆ ለበዓሉ ዝግጁ መደረጉን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡
 
የመምሪያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ልዕልና አበበ እንደገለጹት፤ የጥገና ስራ የተከናወነለት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ ሁለት ሜትር ጥልቀት አለው፡፡
 
የጥምቀተ ባሕሩን የውኃ ስርገት ለመከላከል የሚያስችል የጥገና ስራ መከናወኑንና አሁን ላይም ከ10 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ የመሙላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
በጥምቀተ ባሕሩ መንበረ ታቦታቱ የሚያርፉባቸው ስፍራዎችን የማጽዳትና ለምዕመናኑ ምቹ የማድረግ ስራዎች በአብዛኛው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በበዓሉ የሚታደሙ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችን ጨምሮ ለታላላቅ እንግዶች የሚውሉ የማረፊያ ስፍራዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
እስከ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚያስችሉ የብረት አግዳሚ ወንበሮች ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ተሰርተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል፡፡
 
ክብረ በዓሉን በቀጥታ ስርጭት ለሀገር ውስጥና ለመላው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ጊዜያዊ የቴሌቪዠን ማሰራጫ ስቱዲዮዎች የሚተከሉባቸው ስፍራዎች መደራጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
 
ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ፣የውኃና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን የማሟላት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ዘንድሮ በከተማው በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ጨምሮ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top