እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

2 Days Ago 231
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ጥምቀት፣ ከሰማየ ሰማያት ወረደ፣ በባሕር መካከልም ቆመ ብለን የምናከብረው በዓል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ማድረግ ያለብንን አራት ነገሮች አስተምሮናል።

እነዚህም ወደ ሕዝቡ መውረድ፣ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ማድረግ እና ዓላማን ብቻ መመልከት ናቸዉ።

አንደኛ የሕዝብን ችግር ለመፍታት ወደ ሕዝብ መውረድ ያስፈልጋል። የሕዝብን ፈተና በሪፖርት መስማት ሳይሆን ወርዶ ማየትና መቅመስ ያስፈልጋል። በየአካባቢው፣ በየፕሮጀክቱ፣ በየማኅበረሰቡ እየሄድን ለማየት የምንሞክረውም ለዚህ ነው።

ሁለተኛዉ የሕዝብን ችግር ለመፍታት ራስን አሳልፎ መስጠት ነዉ። በጎችን ለማዳን መፍትሔዉ በጎችን መሠዋት አይደለም። በጎችን ለመታደግ ራስን መሠዋት እንጂ። የሕዝብን ችግር ለመፍታት ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ዕውቀትን፣ መሠዋት ያስፈልጋል። የዕረፍት ሰዓትን፣ የድካም ውጤትን መሠዋት። በመደመር መጽሐፍ ሽያጭ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችም የዚህ ምሳሌዎች ናቸው።

ሶስተኛዉ በምንፈልገውና በሚያስፈልገን መካከል ብዙ ጊዜ ልዩነት አለ። የመንግሥት ዋና ተግባር በጥናት ተመሥርቶ፣ ዐቅሙን አደራጅቶ ለሕዝብ የሚያስፈልገውን መሥራት ነው።

እሥራኤል ክርስቶስ እንዲነግሥ ይፈልጉ ነበር። እርሱ ግን በከብቶች በረት ተወለደ። እንዲዋጋ ይፈልጉ ነበር። እርሱ ግን ሰላማዊ ሆኖ መጣ።  የሚፈልጉትን ሳይሆን የሚያስፈልጋቸውን አደረገ።

ከልደት እስከ ጥምቀት፣ ከጥምቀት እስከ ስቅለት ብዙ ፈተናዎች አሉ። በኃይል፣ በማባበል፣ በማታለል፣ እንደ ወዳጅ በመቅረብ፣ በከንቱ ውዳሴ፣ ብዙ ፈተናዎች ቀርበዋል። ክርስቶስ ግን የሰውን ልጅ ማዳን ነበር ዓላማው። ከጽንሰት እስከ ዕርገት የፈጸማቸው ሥራዎች ሁሉ ዓላማቸው ድኅነት ነው።

አራተኛዉ ከግራ ከቀኝ፣ ከፊት ከኋላ ብዙ መጎተቻዎች አሉ። ብዙ ማሳሳቻዎች አሉ። ብዙ ማሰናከያዎች አሉ። ብዙ ማስፈራሪያዎች አሉ። ግን ከዓላማችን ዝንፍ አንልም። ዓላማችን ሕዝቡን ከድህነት ማውጣት ነው። ኢትዮጵያን ወደ ልዕልና ማድረስ ነው። ኢትዮጵያን ማበልጸግ ነው።

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል የምናከብረው እነዚህን ትምህርቶች እየወሰድን ነው።

መልካም በዓል ይሁንልን።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top