ዛሬ ቃለ መሃላ ፈጽመው 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሚሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ምርጫ ፉክክር ከመግባታቸው በፊት ፕሮጀክት 2025 የሚል ትልቅ ሰነድ አዘጋጅተው ነው የምርጫ ቅስቀሳቸውን ያካሄዱት። አጃንዳ 2025 ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡ ሊያከናውኗቸው ባሰቧቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። በውጭ ጉዳይ ረገድ ሊከተሉት ያሰቡት ሮድማፕ የተካተተበት ይህ ሰነድ ለአፍሪካ ምን አንድምታ አለው?
"ቅድሚያ ለአሜሪካ" የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ በፕሮጀክት 2025 የዩናይትድ ስቴትስን ሀገራዊ ጥቅሞች እና ሀገራቸው በውጭ ግንኙነት ላይ የሚኖራት አቅጣጫ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። በዚህ ፕሮጀክት ከአፍሪካ ጋር በፀጥታና በኢኮኖሚ ግንኙነት የሚኖራቸውን አቅጣጫ ያስቀመጡበት ነው። ይህም ሆኖ ፕሮጀክቱ ላይ በዝርዝር ያልተቀመጡ እና ሥራ ሲጀምሩ የሚያሻሽሏቸው ፖሊሲዎች እንደሚኖሩ በግልጽ ተቀምጧል። ሰነዱ በእርሳቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን አፍሪካን እንደ ቻይና ካሉ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪዎች ተፅዕኖ ለማላቀቅ ሊሠሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል።
ፕሮጀክት 2025 ቀጣዩ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር የተሟላ የመንግሥትነት አገልግሎቱን የሚሰጥበት ፍኖታ ካርታ ነው። ይህ ሰነድ የተዘጋጀው በ‘ዘ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን’ ነው። ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን በአሜሪካ ቀኝ ዘመም አስተሳሰብን ከሚያራምዱ ታዋቂ ቲንክ ታንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ሮናልድ ሬገን ሥልጣን ሊይዙ በነበረበት እ.ኤ.አ በ1981 ለሪፐብሊካን አስተዳደር ፖሊሲ በማውጣት ይታወቃል።
ይህ የትራምፕ አስተዳደር ሰፊ እቅድ ባለ 922 ገጽ የፖሊሲ አጀንዳ፣ የሰራተኛ መመሪያ፣ የሥልጠና ፕሮግራሞች እንዲሁም የአስፈጻሚ ሥልጣንን በማጠናከር የፌዴራል መንግሥትን መልሶ ለማዋቀር የሚያገለግል የ180 ቀናት የትግበራ መርሐ ግብርም የተካተተበት ነው።
ፕሮጀክቱ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሥርዓት ውስጥ ያሉትን የሦስቱ የመንግሥት አካላት ‘ቼክ ኤንድ ባላንስ’ ባህልን በማዳከም የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን ከፍ የሚያደርግ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።
አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶችን ማጠፍ፣ ገደብ የለሽ የግል መብቶችን ሊገድቡ የሚችሉ ፖሊሲዎችን ማውጣት እና የግለሰቦች የበዛ ተፅዕኖ ያለባቸውን ሕጎች ማሻሻል ከፕሮጀክቱ አንኳር ዓላማዎች መካከል ናቸው።
በፕሮጀክቱ ላይ ፅንስ ማስወረድን የሚከለክሉ፣ ለግብረ ሰዶማውያን መብት ገደብ የሚያበጁ፣ እንደ ኤፍ.ቢ.አይ ያሉ ተቋማት ፖለቲካው ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ የሚያስቀሩ እና ጥብቅ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን ማውጣት እንደሚያስፈልግ በዝርዝር ሰፍሯል።
ፕሮጀክት 2025 ለአፍሪካ ያለው ትርጉም
ፕሮጀክት 2025 በዋናነት የሚያተኩረው በአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ ላይ ቢሆንም፤ አፈጻጸሙ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል ነው።
አሜሪካ ለአፍሪካ ከምትሰጣቸው የውጭ እርዳታዎች ለውርጃ እና ተያያዥ አገልግሎቶች የሚውሉት ሊሰረዙ እንደሚችሉ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። ብዙዎች ግን ይህ እርምጃ በአፍሪካ ሀገራት በሚገኙ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል እያሉ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ያልታሰበ እርግዝና እና አደገኛ ውርጃ ሊስፋፋ ይችላል በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ።
በኢኮኖሚው ረገድ ሲታይ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" አጀንዳን የሚያቀነቅኑት ትራምፕ፤ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ስምምነቶች እና የኢኮኖሚ ሽርክናዎችን እንደገና ሊያጤኑ እንደሚችሉ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ሀገራት ለዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ቅድሚያ በሚሰጠው የትራምፕ ፖሊሲ ምክንያት ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገለጻል።
በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ ለወግ አጥባቂ እሴቶች ትኩረት መስጠት በእርሳቸው ዘመን የሚተገበረው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ከእነዚህ መርሆዎች ጋር የሚጣጣሙ መንግሥታትን የመደገፍ አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችልም ይነገራል።
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ትራምፕ ሥልጣናቸውን ሲረከቡ አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገራት የሚኖራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምን እንደሚመስል በግልፅ መተንበይ እንደማይቻል ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚገልጹት።
በለሚ ታደሰ