በሕገ-ወጥ ድርጊት በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡- የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት

13 Hrs Ago 85
በሕገ-ወጥ ድርጊት በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡- የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት
የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ፤ የፋይናንስ ወንጀሎች በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘርፈ ብዙ እና ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ሕጎችን አውጥታ በመተግባር እንደምትገኝም አመላክቷል፡፡
 
ለአብነትም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 እየተተገበረ መሆኑ ይታወሳል።
 
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የህግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁን አስታውሷል፡፡
 
የንብረት ማስመለስ አዋጁም ሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የወጣው አዋጅ ዓላማ የፋይናንስ ወንጀሎች አትራፊ አለመሆናቸውን በማረጋገጥ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ሁሉን አቀፍ አደጋ መግታት ነው ብሏል፡፡
 
በሌላ በኩል ለጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ጠቅሷል፡፡
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግለሰቦች ህጎችን ለማደናገሪያነት በመጠቀም እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን አካላትን ስም በመጥቀስ በማጭበርበር እና በማስፈራራት ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸው ክትትል በማድረግ የተደረሰበት መሆኑን ገልጿል።
 
በዚህም በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ 3 ግለሰቦች ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡ ሌሎችንም በቁጥጥር ስራ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
 
አገልግሎቱ ከራሱ ምንጮችና ከጥቆማ በሚደርሱት መረጃዎች መሰረት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብሏል።
 
በርካታ ጉዳዮችም በህግ ተይዘው ይገኛሉ ያለው አገልግሎቱ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የሚወስዳቸውን ርምጃዎች የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
 
ህብረተሰቡም ማጭበርበርን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ወንጀል በመፈጸም የሚገኝን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሲመለከት በ9796 ነፃ ስልክ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top