ብልፅግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ማከናወኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት "ከቃል እስከ ባሕል" በሚል መሪ ሐሳብ የሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ ቅድመ ጉባዔ የማጠቃለያ መድረክ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ፓርቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያካሂደውን ሁለተኛ ጉባዔ መነሻ በማድረግ፣ በፓርቲው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም በተለያዩ አካባቢዎች የቅድመ ጉባዔ ውይይቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
በዚሁ የቅድመ ጉባዔ ውይይት በክልሉ በየደረጃው የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተገምግመዋል።
በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ ብልፅግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊነትን በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ትኩረት አድርጎ በመስራት የተመዘገቡ ድሎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።
በክልሉ በማዕድን ፣የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሀቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የገጠሙ ስብራቶችን በመጠገን የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች ማከናወኑን አንስተዋል።
በመጪው ጊዜም ለችግሮች መፍትሄ በመስጠት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማፅናት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።