በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ የተከማቸ ከ12 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከሰባት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን የአስተዳደሩ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በሚፈፅሙ ማደያዎች ላይ ጥብቅና አስተማሪ እርምጃ የመውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የድሬደዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያውን ተከትሎ በከተማው እየተካሄደ የሚገኘውን የነዳጅ አቅርቦትና ግብይት የተመለከተ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጥቷል።
በቢሮው የንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ የሚገኙ ማደያዎች በተሻሻለው የነዳጅ ዋጋ መሠረት ነዳጅን በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።
ነገር ግን አንዳንድ ማደያዎች መንግስት በከፍተኛ ድጎማ የሚያመጣውን ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ እያሰራጩ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።
ችግሩን ለመከላከል እና ነዳጅን በፍትሃዊነት ለታለመለት አላማ ለማዋል የፀጥታና የፍትህ አካላት የተካተቱበት ግብረሃይል ተቋቁሞ የተቀናጀ ክትትል እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚሁ መሰረተ በተደረገ ክትትል እና ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በህገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ከ12 ሺህ 700 ሊትር ቤንዚን መያዙን ተናግረዋል።
ቤንዚኑን በመኖሪያ ቤታቸው የደበቁ እና በህገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ነዳጅን በበርሜል በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጡ የተደረሰባቸው ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ሀላፊዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን ገልጸዋል።