የመኸር አዝመራን በጥራት እና በወቅቱ በመሰብሰብ ምርትን ከብክነት ለማዳን፣ በሌላ በኩል የበጋ የመስኖ ግብርናን ካለፉት ዓመታት በተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመኸር አዝመራ ያለብክነት እየተሰበሰበ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ባደረጉት ርብርብ እና የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የመኸር አዝመራው በውጤታማነት እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እስከ ጥር መጀመሪያም በዘር ከተሸፈነው 20.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 18.3 ሚሊዮን ሄክታር መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህም ከ420.2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ ማሰራጨት መቻሉ፣ የግብርና ክላስተር አሠራር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱ፣ የተስተካከለው የዝናብ ወቅት እና በየደረጃው ባሉ ባለድርሻ አካላት የተደረገው ርብርብ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በዳግም ሰብል ምርት 517 ሺህ 663 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ገልጸዋል።
ካለፉት ዓመታት የተሻለ የመስኖ አፈጻጸም እንዲኖር በየደረጃው ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዝግጅት ምዕራፍም የማሳ ዝግጅት፣ የመስኖ ካናሎች ጠረጋ እና ጥገና በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ለመስኖ እርሻው የሚያስፈልገው ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችም በሁሉም አካባቢ እየደረሱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በዚህም በስንዴ ምርት ራሳችንን የመቻል ትልማችንን ለማሳካት የመስኖ እምቅ አቅም ባላቸው አሥር ክልሎች 4.27 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 172.9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታም በባህላዊ 2.7 ሚሊዮን ሄክታር፣ በትራክተር 735 ሺህ 606 ሄክታር መሬት ታርሶ፣ 3.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
ይህም ከክረምቱ የአዝመራ ወቅት ከተገኘው ምርት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የነደፈችውን ግብ ለማሳካት መሰረት እንደሚጥል ይታመናል ብለዋል።
የመስኖ ሥራውን በቀጣይነት ለማስፋትም ትላልቅ የመስኖ ግድብ ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመላው ሀገሪቱ የተጀመሩት የሌማት ትሩፋት እና የከተማ ግብርና ሥራዎች ሌላው የበጋ ወቅት ትኩረቶች እንደሆኑ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ከተረጂነት የሚያላቅቁ ኢኒሼቲቮች፣ በቤተሰብ ደረጃ ጥሪት መፍጠሪያ ስልቶች እና አደጋን የመከላከል እንዲሁም አደጋ ሲያጋጥም በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት አቅሞች ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።