በመዲናዋ ለከተራና የጥምቀት በዓል የሁሉም ታቦታት ማደሪያ ቦታዎች ጽዳት እየተካሄደ ነው

19 Hrs Ago 75
በመዲናዋ ለከተራና የጥምቀት በዓል የሁሉም ታቦታት ማደሪያ ቦታዎች ጽዳት እየተካሄደ ነው
በመዲናዋ ለከተራና የጥምቀት በዓል በሁሉም የታቦታት ማደሪያ ቦታዎች የጽዳት መርሐ ግብር እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገልጸዋል።
 
በጃን ሜዳም "የጥምቀት በዓል በፅዱ አዲስ አበባ" በሚል መሪ ሀሳብ የፅዳት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
 
በመርሐ ግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፣የሁሉም ሃይማኖቶች ተወካዮች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣የአበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤በዓሉን ለማክበር ወደ ከተራና ጥምቀት ለሚጓዙ እግረኞችና ለተሽከርካሪዎች መንገዶችን የማስተካከል ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
 
አዲስ አበባን ውብና ፅዱ የማድረግ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠውም ነው የገለጹት።
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደኢየሱስ ሰይፉ፥ የጥምቀት በዓል ፍቅርንና አብሮነትን የሚያስተምር ነው ብለዋል።
 
የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በአብሮነት በማጽዳት የተባበሩትን የሁሉንም ሃይማኖት ተወካዮችና የህብረተሰብ ክፍሎች አመስግነዋል።
 
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፥ ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉም ህብረተሰብ አንድነቱንና ትብብሩን የሚያጠናክርባቸው መልካም እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።
 
ይህም በዓላቱ ደምቀውና አምረው እንዲከበሩ በማድረግ የሀገር ገፅታ እየገነባ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በዛሬው ዕለትም የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች አንድነታቸውን ለማሳየት በጥምቀት በዓል የታቦታት ማደሪያ የፅዳት ዘመቻ ላይ በመሣተፋቸው ምስጋና አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top