በሀገሪቱ ያለፉ ቁርሾዎችንና ስብራቶችን የሚጠግን፣ በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህልን የሚያጎለብት መደላድል እየተፈጠረ ነው

12 Hrs Ago 83
በሀገሪቱ ያለፉ ቁርሾዎችንና ስብራቶችን የሚጠግን፣ በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህልን የሚያጎለብት መደላድል እየተፈጠረ ነው
የሰላምን አማራጭ የተከተሉ የትኞቹም ቡድኖች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ጥረት በንቃት እንዲሳተፉና የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት አለው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
 
ለሰላም አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ሀገሪቱ በያዘችው የሰላምና የብልጽግና ጉዞ ሂደት ውስጥ ሊጫወቱ የሚችሉትን ወሳኝ ሚና መንግሥት ይገነዘባል ብለዋል ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)።
 
የሰላም አማራጭን በመቀበል ለሚገቡ የትኞቹም ቡድኖች ዛሬም በሩ ክፍት ነው፤ ለዚህም መንግሥት ጥሪውን በድጋሚ ያስተላልፋል ብለዋል ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።
 
የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍና የሚያግባባ፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣ ብዝኃነትንና አንድነትን የሚያሳልጥ፣ በብሔራዊ ትርክት ላይ የተመሰረተ ሀገረ መንግሥት ለመመስረት ጥረት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
 
ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማትን በመገንባት ትውልድ ተሻጋሪና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፤ በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘበት ነው ብለዋል።
 
በሀገሪቱ ያለፉ ቁርሾዎችንና ስብራቶችን የሚጠግን፣ በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህልን የሚያጎለብት፣ የሽግግር ፍትህን መተግበር የሚያስችል መደላድል እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።
 
ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአብዛኞቹ የሀገራችን ክልሎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመምከር አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ አከናውኗል ብለዋል።
 
በቀሪዎቹ የአማራና የትግራይ ክልሎችም ተመሳሳይ ስራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)።
 
መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዜጎችም እንደተለመደው የድርሻቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
 
በመሐመድ ፊጣሞ
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top