ኢትዮጵያ እና ተመድ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

11 Hrs Ago 84
ኢትዮጵያ እና ተመድ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
 
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ጋር በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
 
ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች፣ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባዔ አስመልክቶ እያደረገች ባለው ዝግጅት ላይም መክረዋል።
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቡድን (UNCT) እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ መደገፍ የሚያስችል ግልጽ የኃላፊነት ተዋረድ መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል።
 
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የልማት ግቦቹን አፈጻጸም ለማሻሻል የቀየሰቻቸውን ስትራቴጂዎች አስመልክቶ ለምክትል ዋና ፀሐፊዋ ገለጻ አድርገው፤ ለግቦቹ መሳካት ጠንካራ ትብብር እና ለትግበራው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የልማት ግቦች እንዲሳኩ እያደረጉት ላለው ያላሰለሰ ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
 
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት እና አደረጃጀቶች የዘላቂ ልማት ግቦችን እንደ ሀገር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር አጣጥሞ ማስኬድ ወሳኝ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በዓለም መድረክ የአፍሪካ ልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top