ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከነበሩበት ውጥረት ወጥተው አዲስ ምዕራፍ መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገልጸዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግኑኝነት ለማጠንከርና በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአንካራው ስምምነት እንዲሁም በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ ከተደረጉ መግባባቶች በኋላ ሁለቱ ሀገራት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገራቸውን አንስተዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ መሃሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ መምጣታቸውም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መያዙን ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ቆየት ያለ ግንኙነት እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰው፤ በድንበር፣ በታሪክ እንዲሁም በባሕል የሚተሳሰሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ሀገራቱ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ባደረጉት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ውጤት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም የዲፕሎማሲ ትብራራቸውን ወደ ነበረበት ለመመለስና ለማስቀጠል የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ስኬት መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
"በጋራ መልማት ይገባናል" የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ወንድማማች የሆኑ ህዝቦች በጋራ ማደግ እንዲችሉ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ፣ በጋራ ደህንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ላይም በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም አክለዋል።