የኢትዮጵያ የልማት ድርጅቶች በኢኮኖሚው እድገት ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አጥጋቢ ካልሆነ የአስተዳደር ማእቀፍ በመውጣት፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን እና ወደ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭነት መሸጋገራቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በስሩ 34 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌ ቴሌኮም ፣የኢትዮጵያ ፖስታ ፣የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ፣የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከድርጅቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
በ2014 ዓ.ም በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው ተቋሙ፤ መንግስት ባደረጋቸው ማሻሻያዎች አማካኝነት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ "ኢትዮጵያን ኢን ፎከስ" በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ገልጸዋል።
በፓሪስ የአክሲዮን ገበያ የዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎችን አክሲዮን ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል።
ድርጅቶቹ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባለቤትነት መተዳደራቸው መንግስት ስትራቴጂካዊ ፍላጎቱን እንዲያሟላ ከማገዛቸውም ባሻገር የማዳበሪያ አቅርቦት፣የኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል መገበያያ፣ የኤሌትሪክ ሐይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከማህበረሰቡ የየእለት እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያላቸው ዘርፎችን የያዘ በመሆኑ ተቋሙ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለው ድርሻ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በመረቁት ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካም ድርሻ በመግዛት የፋብሪካውን የስራ አድማስ ለማስፋ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቢሊዮንች ብር የሚቆጠር ሀብት ያላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ከእዳ ይልቅ ስትራቴጂካዊ ሀብቷ ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ እየተወጣ ያለውን ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።