ኢትዮጵያ ጫናዎቹን ወደ ዕድል በመቀየር ታላቁ ሕዳሴ ግድብን አሁን ላለበት ደረጃ አብቅታለች ሲሉ አምባሳደር ኢብራሒም ኢድሪስ ገልጸዋል።
የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሐብት ጉዳዮች ተመራማሪ በዘርፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ አምባሳደር ኢብራሒም ኢድሪስ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" መሰናዶ ላይ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ከተጀመረ በኋላ ከጎረቤት ሀገራትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንደነበሩ አምባሳደር ኢብራሒም አንስተዋል።
ነገርግን ኢትዮጵያ ጫናዎቹን ወደ ዕድል በመቀየር እና ህዝባዊ ተሳትፎችን በማጠናከር አሁን ላለችበት ስኬት መድረሷን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ለረጅም ዘመናት መቆየቷን አስታውሰው፤ በጋራ ተጠቃሚነት መርኋ ከተፋሰሱ ሃገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን በማካሄድ ለድል መብቃቷን ነው የገለጹት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር በበኩላቸው፤ ከጥቅም ጋር በተገናኘ የግድቡ ግንባታ እንዳይካሄድ በተለያየ መልኩ ጫና ሲፈጥሩ የነበሩ ሃገራት መኖራቸውን አስታውሰዋል። ሆኖም ግን በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ትብብር እዚህ ደርሰናል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ባለፉት 6 ዓመታት በመንግስት በተሰጠው ትልቅ ትኩረት እና በተወሰዱ ወሳኝ እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን አመላክተዋል።
በዚህም ከነበረበት ውስብስብ ችግር በመውጣት ማጠናቀቂያ ምዕራፉ ላይ የሚገኘው ግድቡ፣ ግንባታው ከ98 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት።