ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና አካታችነት ያረጋገጠ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ፈዲላ ቢያ ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊዋ የብልፅግና ፓርቲ ምስረታና የፖለቲካ ለውጡ ትሩፋትን በተመለከተ በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" መሰናዶ ላይ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት ለዘመናት ሲንከባለል በመጣ የፖለቲካ ስብራት የዴሞክራሲ እና የእኩልነት ጥያቄ ሳይመለስ መቆየቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ህዝብ በሀገር ጉዳይ እኩል መወሰን የሚችሉበትን እድል የፈጠረ የፖለቲካ አውድ መፈጠሩን አንስተዋል።
በዚህም ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሰሚና ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል ያሉት ኃላፊዋ፤ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጦችን አስመዝግቧል ሲሉ አክለዋል፡፡
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር በቃና አድማሱ በበኩላቸው፤ ለውጡ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ያረጋገጠ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሃገሪቱ ያሉ የተፈጥሮ ሐብቶችን የቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጭምር ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በኅብረ-ብሔራዊነት መሰረት የተመሰረተው የብልፅግና ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያውያንን ፖለቲካዊና የውሳኔ ሰጭነት ተሳትፎ ለማሳደግ የሰራው ስራ ትልቅና የቀደመውን የፖለቲካ ስብራት የቀረፈ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።
የተፈጠረው የፖለቲካ አውድ ሁሉም ክልሎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ እና ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል ብለዋል መምህር በቃና፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በሀገር እና ሰው ተኮር ስራዎች ላይ አተኩሮ በመስራት አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡