የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን በ5 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰነ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ የቀረቡ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ቀሲስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እንዲሁም የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም ተከሳሾቹ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ተከሳሾች በተለያየ መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለባንኩ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህ መልኩ የቀረበውን ዝርዝር ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ የሚጣራ መሆኑን ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።
ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ አጠቃላይ ሦስት ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል መርምሮ በክሱ ዝርዝር የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ማረጋገጡን ጠቅሶ በአንደኛው ክስ ብቻ እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ሁለተኛውን ክስ በሚመለከት በሐሰተኛ ሰነድ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑ በአንደኛው ክስ ላይ መገለጹን ተከትሎ በሰበር ሰሚ ችሎት ትርጉም የተሰጠባቸው በተደራራቢነት የቀረቡና ተጠቃልለው ሊያስቀጡ የሚችሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ፍርድ ቤቱ አብራርቶ ሁለተኛውን ክስ ውድቅ በማድረግ በአንደኛው ክስ ብቻ በከባድ አታላይነት ሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
ሆኖም ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸው ተጠቅሷል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የሀሳብ ልዩነት ያቀረቡት አንደኛው ዳኛ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት የባንክ ሂሳባቸው በመገለጹ ብቻ የወንጀል ተግባሩ በስምምነት ተፈጽሟል ለማለት አያስችልም የሚል የሀሳብ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው ልዩነታቸውን አሳይተዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉ የተፈጸመው በትብብር መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ መያዙን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።
በዚህም1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን ያቀረቡትን አራት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 21 መሰረት በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ እያንዳንዳቸው አራት፣ አራት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በዕርከን 17 መሰረት በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የተወሰነውን የጽኑ እስራት ውሳኔን የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ እንዲያስፈጽም ታዟል።