በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩና በቫይረሱ ምክንያት ችግር ላይ ለሚገኙ አካላት ህክምናና ድጋፍ እንዲያገኙ አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢያ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትረ ስልጣናቸውን በተቀበሉበት ቀን ካስተላለፏቸው ትእዛዞች መካከል አሜሪካ የምትሰጠው ማንኛውም የውጭ እርዳታ ለሚቀጥሉት 3 ወራት እንዲቆም መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
በተለይም ለዓለም ጤና ድርጅት 18 በመቶ የገንዘብ ምንጭ የሆነችው አሜሪካ በ12 ወራት ውስጥ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ለመውጣት መወሰኗ ድርጅቱ “ጤና ለሁሉም” በሚል እየሰራቸው ለሚገኙ ስራዎች ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር እንደሚገጥመው ሲገለፅ ቆይቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢያ ይፋ ባደረጉት መረጃ ሃገሪቱ በ55 ሀገራት ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች እየሰጠች የነበረውን አስቸኳይ ድጋፍ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ለህይወት አድን መድሃኒት መግዣ፤ ለህክምና፣ ለምግብና መጠለያ እንዲሁም በስራው ላይ ለሚገኙ የአስተዳደር ወጪዎች የአሜሪካ ድጋፍ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡
ውሳኔው በ55 ሀገራት ውስጥ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩና ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኤች አይቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡
የድጋፉ መቀጠል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል፤ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች፤ በቫይረሱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት፤ በቫይረሱ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት፤ ለነብስ አድን ስራዎች ድጋፍና እንክብካቤ መስጠቱን ለመቀጠል ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ ለማንኛውም የውጭ ሀገራት የምትሰጠውን ድጋፍ እስከ ሚቀጥሉት 3 ወራት ድረስ በማጥናት በቀጣይ ውሳኔዋን ይፋ እንደምታደርግም ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
የአሜሪካን ውሳኔ ያደነቀው ዩ ኤን ኤድስ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እያደረጋቸው ያሚገኙ ጥረቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡
በላሉ ኢታላ