ዓለም የተገረመበት የአምናው የቱሪዝም ስኬት ምስጢሮች

1 Day Ago 357
ዓለም የተገረመበት የአምናው የቱሪዝም ስኬት ምስጢሮች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቱሪዝም ባሮሜትር መረጃ እንደሚያመላክተው በ2024 ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ተጓዦች ወደ ተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ተጉዘዋል።

ይህ የተጓዦች ቁጥር ከኮቪድ ወረርሽሽኝ በፊት ወደ ነበረው ቁጥር መቃረቡንም የሚያመላክት መሆኑን የድርጅቱ ሪፖርት አመላክቷል።

በዚህ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት ኳታር ከ2019 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ137 በመቶ ዕድገት በማሳየት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ሆናለች፡፡ 

ኢትዮጵያን ጨምሮ ጃፓን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ማልታ፣ ሞሮኮ እና ዶሚኒካን ሪፐብሊክ በተከታይነት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ኖሯቸው በዘርፉ አስደናቂ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል።

ከዚህ በፊት በቱሪስቶች አይን ውስጥ እምብዛም ያልነበረችው ኳታር በ2024 እንዴት የቱሪስቶች መዳረሻ ለመሆን በቃች የሚለው አነጋጋሪ መረጃ ሆኗል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ትራቨል ቱር ወርልድ በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው ሀተታ ኳታር ድምጿን አጥፍታ ነገር ግን አስደናቂ ስራዎችን ሰራታለች ይላል።

በተለይ ደግሞ የዝነኛው የሃማድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በ2022 የፊፋን የዓለም ዋንጫ ማዘጋጀቷ፣ ቅንጡ የቱሪስት ማረፊያዎችን መገንባቷ፣ ባህላዊ እሴቶቿን አጉልታ ማሳየቷ ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንደትቆናጠጥ አስችሏታል ነው የሚለው ትራቭል ቱር ወርልድ።

በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉት ሀገራት በተቃራኒ ሁሉን አቀፍ መዳረሻዎችን ማዘጋጀቷ፣ የጎብኚዎችን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ዝግጅቶችን ማድረጓ፣ ዘመናዊነትን ከወግ ጋር ሳታጣርስ አዋህዳ ማቅረቧ እና ማራኪነቷ ሌላው የስኬቷ ምስጢር ሆኖላታል፡፡

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባቷ፣ ነባሮችን የማዘመኗ፣ በዘርፉ ላይ ያደረገችው ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት እና ምቹ መሰረተ ልማቶችን መገንባቷ ቀድመው ዘርፉን ሲመሩ የነበሩ እነጃፓንን ጭምር እንድትቀድም አስችሏታል።

ይህ የመሪዎቿ የረጅም ጊዜ ራዕይን የሰነቀው ሥራዋ ኳታር የ2024 ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቁንጮ እንድትሆን በማስቻሉ በ2024 ብቻ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በማስተናገድ የዓለም አቀፍ የጉዞ ማዕከልነቷን አረጋግጣለች።

በአንፃሩ ጃፓን 37 ሚሊዮን ጎብኚዎች፣ ቱርክ ከ49 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችን በመሳብ ከፍተኛ ዕድገት ቢያስመዘግቡም ይህ ዕድገታቸው ከኳታር ጋር ሲነፃፀር ግን እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።

በተመሳሳይም ስፔን 10.7 በመቶ እንዲሁም የሞሮኮ 20 በመቶ ዕድገት ቢያስመዘግቡም ከኳታር አስደናቂ ግስጋሴ ጋር ሲነጻጸሩ ግን በጣም ሩቅ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑ አልቀረም፡፡

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ዓለም አቀፍ ቦታዋ የት ነው?

ቱሪዝም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ የተመረጠ ዘርፍ ነው። የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ የሀገር በጎ ገጽታን በማጉላት፣ የኢትዮጵያን የበለፀገ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ለዓለም በማስተዋወቅ፣ እና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ እየተሠራበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዘርፉ ችግሮችን በመፍታት እና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ቱሪዝም ዘላቂና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያለውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ አየሠራች ነው፡፡

እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቱሪዝም ባሮሜትር መረጃ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች።  ይህ አስደናቂ እድገት በታሪክ፣ በባሕል እና በተፈጥሮ ድንቆች የበለፀገ መዳረሻ በመሆን የሀገሪቱ ተወዳጅነት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች በአውሮፓውያኑ 2024 የጎበኟት ኢትዮጵያ፣ በ2030 ቱሪዝም የበለጠ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይሄው መረጃ ሲያመላክት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃትም ግንባር ቀደም መሆን ችላለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

 እንደ ዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ካውንስል ሪፖርት የቱሪዝም ዘርፉ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያበረከተው አስተዋፅኦ 10.4 በመቶ ደርሷል። ይህም 524.7 ቢሊዮን ብር ወይም 9.6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የ16.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ዘርፉ የ2.12 ሚልዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም በሌሎች ዘርፎች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል 6.3 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል።

በዘርፉ እንደዚህ ዓይነት አበረታች ዕድገት እንዲመዘገብ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና የአዳዲስ መዳረሻዎች መስፋፋት ወሳኙን ሚና ተጫውቷል፡፡ የአመራር ቁርጠኝነት ደግሞ ለእነዚህ ሁሉ ቁልፍ ሚና አለው፡፡ መንግሥት በትኩረት የሠራበት ገበታ ለሀገር የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በመቀየር ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። እንደ ኮይሻ፣ ሃላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ሎጅ፣ ጎርጎራን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ሥራ መጀመር መንግሥት ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም መዳሻዎችን ለማልማት ላለው ቁርጠኝነት አመላካች ነው።

ይህ ኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ እየሠራችው ያለው ሥራ የምሥራቅ አፍሪካ በይነመንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን (STMP) 2024-2034 ጋር የሚናበብ ነው፡፡ ይህ የኢጋድ እቅድ ዘላቂነት ባላቸው የቱሪዝም ተግባራት ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን ጨምሮ አካባቢውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት ያለው መዳረሻ ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ዓላማ ለማሳካት ዘርፉ ራሱን ችሎ እንዲቆም ከማድረጉም በላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ የቱሪዝምን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለማሻሻል ስትራቴጂካዊ እቅድ እና ኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን ለማገዝ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ አደርጋለች።

በቀጣይም የዘርፉን ኢንቨስትመንት በማጠናከር ቱሪዝም በየዓመቱ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ እንዲያበረክት እየተሠራ ሲሆን፣ በ2022 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top