የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሆነው የተመረጡት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ማን ናቸው?

9 Hrs Ago 71
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሆነው የተመረጡት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ማን ናቸው?
ዛሬ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሃላ የፈጸሙት አቶ ብርሃኑ የተወለዱት ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነው፡፡
 
ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕንድ ሀገር የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
 
"የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ትግበራ፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች ሚና" በሚል ርዕስ የሠሩት የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያለበትን ኃላፊነቶች ያመላከተ እንደሆነ ይጠቀሳል።
 
በ1997 ዓ.ም ምርጫ የቦንጋን ሕዝብ ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። በተለያዩ መንግሥታዊ የስራ ኃላፊነቶች ላይም ሠርተዋል፡፡
 
በቀድሞው ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፍትሕ ቢሮ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይም አገልግለዋል። የክልሉ ቢሮ የአስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ማገልገል የጀመሩት አቶ ብርሃኑ፤ መስሪያ ቤቱን በምክትል እና በዋና ኃላፊነት መርተዋል።
 
አቶ ብርሃኑ ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል። ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።
 
ታኅሳስ 2007 ዓ.ም ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርነት ከተሰናበቱ በኋላ፣ ከፓርቲም ከመንግሥትም ኃላፊነት በመልቀቅ በግል ሥራቸው ላይ መቆየታቸውን ዛሬ ለፓርላማ በቀረበው የትምህርት እና የስራ ልምድ ዝርዝራቸው ላይ ተጠቅሷል።
 
ከባለፈው ታኅሳስ ወር ጀምሮ የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ሲቀበል የቆየው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከተጠቆሙት ዕጩዎች መካከል አቶ ብርሃኑ አዴሎን ኮሚሽነር አድርጎ ሰይሟል።
 
በለሚ ታደሰ
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top