የጊቤ መንግሥታት ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል ዝነኛ የነበሩ አምስት ሥርዎ መንግሥታት ናቸው።
በበለፀገ ባህላቸው እና የንግድ እንቅስቃሴያቸው ይታወቁ ነበር። በተለይ ምጣኔ ሀብቱ ረገድ ቡና በአካባቢው የኢኮኖሚ መሠረት ነበር። ከጊቤ ግዛቶች አንዱ የሆነው የጅማ መንግሥት ከጊቤ መንግሥታት መካከል ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና እጅግ የበለጸገ እንደነበር ይነሳል::
እነዚህ በጅማ እና አካባቢው የነበሩ አምስቱ የጊቤ መንግሥታት ጅማ፣ ሊሙ-ኢናሪያ፣ ጌራ፣ ጎማ እና ጉማ ይባሉ ነበር፡፡
የጅማ መንግሥት በጂረን (የአሁኗ ጅማ) ከትሞ የነበረ ሲሆን የተመሰረተውም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው::
በአባ ጅፋር መሪነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የጅማ ስልጣኔ በዚያን ዘመን ለም መሬቷ እና በአካባቢው ምቹ የአየር ንብረት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ተመርቶ ወደ ውጭ እንድትልክ አስችሏታል።
በዘመኑ ጅማን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እስከ ቀይ ባሕር የሚያገናኙ የንግድ መስመሮችን በመጠቅም የዓረብ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሃብቶች ጋር የንግድ ልውውጥ እስከማድረግ ተደርሷል::
ይህ የንግድ ግንኙነት ከኢትዮጵያ አልፎ እስከ መካከለኛው ምስራቅ እና የአረብ ሀገራት የዘለቀ ስለነበር ነጋዴዎች ወደ ጅማ በመምጣት በንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት እድሉን አግኝተዋል፡፡
እናም ይህ ግዙፍ የነበረው ስልጣኔ አሻራ ዛሬም በጅማ የሚገኝ ሲሆን የአባ ጅፋር ቤተ-መንግሥት ዋንኛው ታሪካዊ ቅርስ ሆኖ ለዚህ ትውልድ ደርሷል::
ቤተ-መንግሥቱ የተገነባው ከ1870 እስከ 1924 ዓ.ም ድረስ ሲሆን አባ ጅፋር በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን በነበረው ግዛትን የማስፋፋት ዘመቻ የራሳቸውን ግዛት በማስጠበቅ ቀጥለዋል፡፡
አባ ጅፋር ከአጼ ምኒልክ ጋር በመወያየት እና ግዛታቸውን በማስጠበቅ ሕዝቡን ከማይገባ ጦርነት በመታደጋቸውም ይሞገሳሉ፡፡
በብልህ አመራራቸው እና በዲፕሎማሲያዊ ስኬታቸው የሚወደሱት አባ ጅፋር በዘመናቸው የጅማን ዓለም አቀፍ ንግድ ማዕከልነት እንዳጎሉ ታሪካቸው ዋቢ ነው።
በአባ ጅፋር ዘመን የተረጋጋ አስተዳደርን በማስፈን እና ሰላምን ከማፅናት ባሻገር ጅማ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንድታበረክት አስችለዋል::
ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ስትራተጂያዊ ጥምረት እንደነበራቸው የሚነሱት አባጅፋር ግዛታቸው ጅማ ከኢትዮጵያ ግዛቶች አንዷ ሆና ነገር ግን የራሷን ውሳኔዎች እየወሰነች ለሰላም እና ዕድገት እንድትሠራ አስችለዋታል::
ቤተ-መንግሥቱ የኦሮሞን ባህላዊ የቤት አሠራር ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የቤት አሠራር ጥበብ ጋር ያጣመረ እና የዚያን ዘመን የሕንፃ ጥበብ የሚያንጸባርቅ ድንቅ የጠቢባን እጆች ውጤት ነው።
እንጨት እና ጭቃን በመጠቀም የተሰራው ድንቅ ቤተ መንግሥት በዚያን ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያውያን የግንባታ ዘዴን የሚያሳይም ነው።
ከእንጨት በተሠሩ ጌጠኛ ምሰሶዎችን እና ዓምዶች የተሠራው ይህ ቤተ-መንግሥት እንጨቶቹ በብል እንዳይበሉ የተደረገበት ጥበብ ሌላ ጥናት የሚያስፈልገው ነው።
ቤተ መንግሥቱ ለንጉሡ እና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ፣ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች እና ለእንግዶች የሚሆኑ በቂ እና ምቹ ክፍሎች ይዞ የተገነባ ነው::
መንግሥታዊ ጉዳዮች እና ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚደረግበት ‘ጉዶ’ የተባለ ታላቅ አዳራሽ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ይገኛል፡፡ ‘ጉዶ (guddoo)’ የአፋን ኦሮሞ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ትልቅ ማለት ነው፡፡
ቤተ-መንግስቱ በጅማ እና አካባቢው የነበሩትን የጊቤ መንግሥታት ታሪክ እና ባህል እንዲሁም የአባ ጅፋር ጥበብን የሚያሳይ የታሪክ ምስክር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የንጉሡን ሕይወት እና በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማስተዋል የሚያስችሉ ቅርሶችን፣ የንጉሳውያንን ታሪክ እና ፎቶግራፎችንም ይዟል::
የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ለረጅም ጊዜ ባለመታደሱ ምክንያት ለአደጋ ተገልጦ ቆይቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እድሳት እየተደረገለት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየተገባደደ ያለውን የቤተመንግሥቱን ዕድሳት ጎብኝተዋል::
በለሚ ታደሰ