በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ የተቀበሉት አሜሪካዊው ሴናተር የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው

16 Hrs Ago 93
በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ የተቀበሉት አሜሪካዊው ሴናተር የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ የግብፅን ጥቅም ለማስጠበቅ ጉቦ የተቀበሉት የቀድሞው የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
 
ቦብ ሜኔንዴዝ የግብፅን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ የዓይነት ጉቦ መቀባላቸው በመረጋገጡ ነው እስራቱ የተፈረደባቸው።
 
የአሜሪካን ሕዝብ ከወከለ እንደሳቸው ዓይነት ሰው በማይጠበቅ መልኩ ሌላ ሀገርን በመርዳት 16 ክሶች የቀረቡባቸው ሜኔንዴዝ፣ ይህም ቢያንስ 15 ዓመታት ሊያስፈርድባቸው እንደሚገባ ዐቃቤ ሕግ ክርክር አቅርቦ እንደነበር የቢቢሲ መረጃ ያመላክታል።
 
በተለይም ከግብፅ መንግሥት የተቀበሏቸው ጥፍጥፍ ወርቆች፣ ጥሬ ገንዘብ እና መርሴዲስ ቤንዝ መኪና ለወንጀላቸው ማረጋገጫ ተደርገው ለፍርድ ቤት ቀርበዋል።
 
ሜኔንዴዝ በጠበቃቸው በኩል ቀለል ያለ የማኅበራዊ አገልግሎት ቅጣት እንዲጣልባቸው ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ግን የ11 ዓመታት እስራት ፈርዶባቸዋል።
 
በተያያዘም ረቡዕ ዕለት ሁለት የሜኔንዴዝ ተባባሪዎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
 
በኒው ጀርዚ የሪል እስቴት አልሚ የሆነው እና ለሴናተሩ ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ እንደሰጠ የተነገረለት ፍሬድ ዳይቤስ የ7 ዓመት እስራት እና 1.75 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥቷል።
 
ሜኔንዴዝን ከግብፅ መንግሥት ጋር በማገናኘት ወንጀል የተሳተፈ ዋኤል ሃና የተባለ ግብጻዊ-አሜሪካዊ ነጋዴም ከስምንት ዓመት በላይ እስራት እና የ1.25 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተወስኖበታል።
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top