በዓለም ላይ የማን ሀገር ገንዘብ ነው ጠንካራ ወይም በምንዛሬ ከፍተኛ የሚባለው?

1 Day Ago 114
በዓለም ላይ የማን ሀገር ገንዘብ ነው ጠንካራ ወይም በምንዛሬ ከፍተኛ የሚባለው?

ብዙ ሰው ጠንካራ የሚባል ገንዘብ ምንድነው ወይም የቱ ነው ተብሎ ቢጠይ የአሜሪካ ዶላር ወይም የእንግሊዝ ፓውንድ ሊል እንደሚችል ይገመታል። በተል ዶላር በዓለም ላይ የመገበያያ ገንዘብ በመሆኑ በብዙ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለው ቦታ በብዙ መልኩ ነው።

ለመሆኑ በዓለም ላይ ጠንካራ ገንዘብ ካላቸው ሀገራት መካከል እርስዎ ጥቀሱ ቢባሉ የማንን ይጠቅሳሉ? ለማንኛውም የዓለማችን ጠንካራው ገንዘብ የማነው የሚለውን እንመልከት።

የኩዌት ዲናር (KWD) በዓለም ላይ እጅግ ጠንካራው ምንዛሬ ያለው ገንዘብ ነው። በዛሬው ዕለት በሀገራችን ባንኮች ባለው የውጭ ምንዛሬ መሰረት የኩዌት ዲናር ከአሜሪካ ዶላር፣ ከዩሮ እና ከእንግሊዝ ፓውንድ ጋር ብናነጻጽረው ከአሜሪካን ዶላር በ218 በመቶ፣ ከዩሮ በ207 በመቶ እንዲሁም ከእንግሊዝ ፓውንድ በ159 በመቶ ገደማ ይበልጣል፡፡ አንድ የኩዌት ዲናር በ3.2 የአሜሪካን ዶላር አካባቢ ይመነዘራል፡፡

ጠንካራ ገንዘብ ማለት ከሌሎች ገንዘቦች ሁሉ የላቀ የመግዛት ኃይል ያለው ነው። አንድ ጠንካራ ገንዘብ ከሌላው ጋር ሲነጻጸር የመግዛት አቅሙ የተሻለ ሲሆን ምንዛሬውም እንደዚያው ጠንካራ ይሆናል፡፡ የኩዌት ዲናር በዚህ ረገድ በ2025 ጠንካራ ተብለው ከተዘረዘሩት የ25 ሀገራት ገንዘቦች መካከል በአንደኛነት ተቀምጧል፡፡

ለመሆኑ ይህ የኩዌት ዲናር በምን ምክንያት ከሌሎቹ ምንዛሬዎች ሊበልጥ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ዋና ዋና ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት እና የኢኮኖሚ መረጋጋት ነው፡፡ ኩዌት ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ካላቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ ዋነኛ የነዳጅ ላኪም ናት። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱን ገቢ የሚሸፍነው ወደ ውጭ የሚላከው ነዳጅ ሲሆን፣ ይህም ጠንካራ እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖራት አድርጓታል። የኩዌት ነዳጅ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ከፍተኛ ደረጃ መፈለጉ ገንዘቧ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል።

የተስተካከለ እና ቋሚ የምንዛሬ ሥርዓት ሌላው የገንዘቧ ጥንካሬ ምክንያት ነው፡፡ ኩዌት በየጊዜው በሚለዋጠው ገበያ የምንዛሬ ዋጋቸውን እንደሚያስተካከሉት ሀገራት አለማድረጓ፣ የዲናሯ ዋጋ የተረጋጋ እና የማይለዋወጥ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም የዲናር ዋጋ ከሌሎች ዋና ዋና ገንዘቦች የተሻለ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል።

ውስን የገንዘብ አቅርቦት ሌላው የዲናር ዋጋ የተረጋጋ እንዲሆን ያደረገ የሀገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ የኩዌት መንግሥት የገንዘብ አቅርቦቱን በጥንቃቄ የሚቆጣጠር ሲሆን፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰትም በየጊዜው ክትትል በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ይከላከላል።

ጠንካራ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በሀገሪቱ መኖሩ ሌላው የዲናርን ጠንካራነት ያስቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ ኩዌት በወርቅ፣ ቦንድ እና በውጭ የተከማቸ መዋዕለ ንዋይን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አላት። እንደዚህ ዓይነቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እና ሀገሪቱ ያላት የእሴት ክምችት የዲናርን ጠንካራነት አስቀጥለዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በሚኖርበት ጊዜም እንኳ ዲናር ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ አድርጓል።

አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) እና የነፍስ ወከፍ ገቢዋም ለገንዘቧ ጠንካራነት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ያለፈው የፈረንጆች ዓመት የኩዌት የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ30 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ነበር፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ባለጸጋ ከሆኑት ሀገሮች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል። ጠንካራ ኢኮኖሚ እና ዝቅተኛ ሥራ አጥነትም ለገንዘቡ ጥንካሬ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በጣም ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበትም ዲናርን ጠንካራ አድርጎታል፡፡ ኩዌት የለም የሚያስብል በጣም ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት ያላት ሲሆን፣ ይህም ገንዘቧ በጊዜ ሂደት ዋጋውን እንዳያጣ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ዲናር ለንግድ እና ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ተፈላጊ ሆኖ ቀጥሏል።

የሀገሪቱ መንግሥት የሚከተለው ጠንካራ የባንክ ሥርዓት እና የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችም የዲናርን ዋጋ ጠንካራ አድርጎታል፡፡ የኩዌት ማዕከላዊ ባንክ የተረጋጋ የገንዘብ ፍሰትን ለማስጠበቅ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ይከተላል። የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሀብት ፈንድ (የኩዌት ኢንቨስትመንት ባለስልጣን - KIA) በዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ኢኮኖሚውን የሚያረጋጋ ሥራ መሥራቱን ቀጥሏል።

የኩዌት ዲናር ጥንካሬ ምንጭ ከነዳጅ ሀብት ያለፈም እንደሆ ይነገራል፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት በነዳጅ የሚገኘውን ሀብት በተለያዩ ሀገራት ኢንቨስት በማድረግ በቀጣይ የነዳጅ ተፈላጊነት ዝቅ ቢል ከቀውስ መውጫ መንገድ አዘጋጅቷል፡፡ ከሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውጭም እንደ ቱሪዝም ያሉትን አማራጮች በማስፋት የኩዌት ኢኮኖሚ በነዳጅ ሀብት ብቻ ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዳይቀር እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፀና መሰረት ላይ እንዲቆም እየሠራ ነው፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top