ኢትዮጵያን ጨምሮ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት የዱባይ ፖሊሳዊ ውድድር ምንድነው?

2 Mons Ago 911
ኢትዮጵያን ጨምሮ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት የዱባይ ፖሊሳዊ ውድድር ምንድነው?

ዓለም አቀፍ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን (SWAT) ውድድር በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚዘጋጅ ዓመታዊ ወድድር ነው፡፡ ይህ ክንውን ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ስልታዊ ቡድኖችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ችሎታቸውን፣ ጽናታቸውን፣ የቡድን ሥራቸውን እና ሌሎች ወሳኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙአቸው ምላሽ ለመስጠት ያላቸውን ችሎታ በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲፎካከሩ ያደርጋል።

መርሐ ግብሩ የተጀመረው በ2019 በዱባይ ፖሊስ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የሕግ አስከባሪነት እና ስልታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስፋፋት ወሳኝ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ተደርጓል።

ዓላማውም ዓለም አቀፍ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኖችን የሥልጠና ደረጃ ማሻሻል ነው። በተለይ በከተሞች እና ስልታዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የእውቀት እና ክህሎት ሽግግር እንዲኖር ያስችላል። በተጨማሪም ሽብርተኝነትን፣ የተደራጀ ወንጀልን እና ሌሎች ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጡ ስጋቶችን በመዋጋት ረገድ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከርም ያገለግላል።

ይህ ዝግጅት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ የአውሮፓን እና የመካከለኛውን ምሥራቅ ሀገራትን ጨምሮ ከ48 ሀገራት የተውጣጡ ቡድኖችን የሚያሳትፍ ነው። በእነዚህ ተሳታፊዎች መካከልም ፉክክር ይደረጋል፣ የልምድ ልውውጥም ይካሄዳል፡፡

በእውነተኛ የሥራ ሕይወት ውስጥ በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ውስጥ የሚደረግ ሲሆን፣ መሰናክል፣ ታክቲካዊ ህይወት ማዳን ሥራዎች፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ፣ ታክቲካዊ ጥቃት መፈጸም፣ ጥቃትን በመከላከል እና በቡድን ሥራ ላይ ፉክክር ይካሄዳል፡፡

ዝግጅቱ በአውሮፓውያኑ 2019 ሲጀምር ከዓለም ዙሪያ ከ50 የሚበልጡ ቡድኖች ተሳትፈውበት በስኬት ተጠናቅቋል። እግረ መንገዱንም ዱባይ ከፍተኛ ግምት ያላቸው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ዝግጅቶችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት አሳይቷል። ከዚያን ወዲህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዋና ዋና ስልታዊ ውድድሮች አንዱ ሆኖ እውቅና በማግኘት ዓመታዊ ክንውን ሆኖ ቀጥሏል።

አሁን ላይ ተሳትፎው እየሰፋ መጥቶ ባለፈው ዓመት ከ60 የሚበልጡ ቡድኖች ተፎካክረውበታል። በዚህ የዱባይ ፖሊስ የድሮን፣ የሮቦት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንዴት በስልታዊ መንገድ አየተጠቀመ እንደሚገኝ ሥልጠና እና ልምዱን አካፍሏል።

ይህ መርሐ ግብር ከውድድርም በላይ ሲሆን፣ የህግ አስፈፃሚ አካላት ኔትወርክን ለማሳደግ፣ ተሞክሮዎችን ለማጋራት እና የሥራ ቅልጥፍናን ለማሻሻል የሚያስችል መድረክ ነው። ዱባይ በህግ ማስከበር ውስጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማካተት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት እና ለሌሎችም ልምድ የምታካፍልበት ነው።

መድረኩ በሕግ አስከባሪነት ረገድ ጥሩ ችሎታን በማሳየት እና አዳዲስ ነገሮችን በማከናወን ራስን ለቀጣይ ግዳጅ ለማዘጋጀት ዓይን ከፋች እንደሆነ ይነገርለታል።

በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው የደኅንነት ሁኔታ ውስጥ ለሚፈጠሩ አደጋዎች ዝግጁ ለመሆንም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ነው የሚጠቀሰው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን (SWAT) በዘንድሮው መድረክ ላይ ለመሳተፍ  ወደ ዱባይ አቅንቷል። ቡድኑ በታክቲካል ኦፕሬሽን ቻሌንጅ፣ በጥቃት ቻሌንጅ፣ በVIP አመራር የማዳን ተልዕኮ፣ በከፍተኛ ታወር መውጣትና መውረድ እና በመሰናክል ኮርስ ይወዳደራል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ቡድኑን በሸኙበት ወቅት ተወዳድሮ ከማሸነፍ ባለፈ በፈጣን ምላሽ ሰጭነት ላይ ተሞክሮውን ለማካፈል፣ ከዓለም አቀፍ ልምምዶች ጋር ለመተዋወቅ፣ ከተለያዩ ሀገራት ጥሩ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እና ዝግጁነቱን የበለጠ ለማሳደግ ውድድሩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በውድድሩ ላይ መልካም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር በማሳየት በብቃት ተወዳድራችሁ በአሸናፊነት የሀገራችንን እና የተቋማችንን መልካም ገጽታ በዓለም መድረክ ላይ እንድታስተዋውቁ በማለት የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top