አፍሪካዊው ማራዶና - አቢዲ ፔሌ

23 Hrs Ago 488
አፍሪካዊው ማራዶና - አቢዲ ፔሌ

. በሀሰት የህክምና ምርመራ ዝውውሩ የታገደ ጊዜ


ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወይንም ሊዮኔል  ሜሲ እና ኔይማር ከእግር ኳስ ጀርባ ተሰራ በተባለ ሴራ ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ ስማቸው ተነስቶ  ሊሆን ይችላል፡፡ አልያም ክለቦችም ይሁኑ ሀገራት የጨዋታ ውጤት ለማስቀየር ከመጋረጃ ጀርባ በብዙ ሴራ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል::


እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች  ግን ከዚህኛው ፊት ከምንም የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡  በ1980ዎቹ አጋማሽ አውሮፓ ላይ ያለ አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ክለብ ከአፍሪካ  የምንጊዜም  ከዋክብት  አንዱ  የሆነውን ተጫዋች አቢዲ ፔሌ ላይ የሰራው  በደል  ነው፡፡ 

እርግጥ ነው ከጾታዊ ትንኮሳ እና ከሰነድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ብዙ ተጫዋቾች ባልዋሉበት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል:: ነገሩ አፍሪካውያን ላይ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ሌላ መልክ ይይዛል፡፡


በተለይ የዝውውር ጉዳዮች ሲነሱ ክለቦች የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ለማስፈረም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይጓዙት ርቀት የለም፡፡ ተጫዋቾችን በጥቅማጥቅም ከመደለል እስከ ዘለግ ያለ ደመወዝ ማቅረብ እና ሌሎችም፡፡

በ1987 የፈረንሳዩ ክለብ ኦሎምፒክ ደ ማርሴ ጋናዊውን አቢዲ ፔሌን ለማስፈረም የተጓዘበት መንገድ ግን ሊፈጸም ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡ ነገሩ ካለፈ በኋላ ብዙዎች ጉዳዩን ከራስ ወዳድነት ያለፈ ሰብአዊነትን ጭምር የሚጋፋ ክብረ ነክ ነው ይሉታል፡፡

 
ከፈረንሳዩ ክለብ ኒዮርት ወደ ሌላኛው የፈረንሳይ ክለብ  ሙልሆዝ ካመራ በኋላ ብቃቱን በሚገባ ማሳየት የቻለው አቢዲ ፔሌ በታላላቅ  የአውሮፓ ክለቦች አይን ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ሞናኮ እና ማርሴ ደግሞ የወቅቱን የአፍሪካ ፈርጥ ለማስፈረም ፍላጎት ያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ ይፋዊ ጥያቄ  አቀረቡ፡፡ 

 ነገር ግን በወቅቱ ከማርሴይ ይልቅ ሞናኮ የተሻለ የዝውውር ገንዘብ በማቅረቡ ሙልሆዝ አማካዩን ለሞናኮ ለመሸጥ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ አቢዲ ፔሌ  ወደ ሞናኮ የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ  ስምምነት ላይ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን በይፋ የሞናኮን መለያ ለመልበስ አንድ ነገር ይቀረዋል፡፡ የህክምና ምርመራውን ማጠቀናቀቅ :: የጉዳዩ ሴራ የሚጀምረውም እዚህ ጋር ነው፡፡ 

ጋናዊውን ኮከብ ከሞናኮ ጋር ተፎካክሮ ማስፈረም እንደማይችል የገባው ኦሎምፒክ ደ ማርሴ በፕሬዝደንቱ በርናርድ ታፒ በኩል ሌላ መንገድ ይፈልጋል፡፡ ከምርመራው በፊት ተጫዋቹ ኤች አይ ቪ እንዳለበት በማስመሰል በሞናኮ አካባቢ እንዲወራ ያደረጉት አወዛጋቢው፣ ፖለቲከኛው እና ባለሀብቱ ሰው በርናርድ ቴፒ የመሀል ሜዳ ሞተሩን የግላቸው ለማድረግ በተጨማሪም የሞናኮ የሕክምና ዶክተሮችን እና የክለቡን ሃላፊዎች በገንዘብ በመደለል የሕክምና ውጤቱ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ 

 

የጨዋታ ውጤትን በገንዘባቸው ከማስቀየር ጀምሮ ግብር  በመሰወር በተደጋጋሚ ሰማቸው ይነሳ የነበረው የማርሴ ፕሬዝደንት ከፈሉት በተባለው ገንዘብ የአቢዲ ፔሌን የህክምና ውጤት አስቀየሩት፡፡ በደሙ ውስጥ ኤች አይ ቪ እንዳለበት የሚያረጋግጥ የሀሰት ማስረጃ አሰርተው አጠናቀቁ፡፡ የሞናኮ ሰዎችም በህክምና ውጤቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ከዝውውሩ አገለሉ፡፡ ዝውውሩም ተቋረጠ፡፡

በሴራ ጠንሳሹ ሰው ምክንያት በሞናኮ ያልተፈለገው ፔሌ ፊቱን ወደ ማርሴ አዞረ :: የቴፒ  ዕቅዳቸው ሰምሮላቸው  ተጫዋቹን የግላቸው አደረጉት፡፡ ምንም እንኳን አቢዲ ፔሌ በእንዲህ አይነት ውስብስብ ሂደት የማርሴ ንብረት መሆኑ ከህግም ከሰብአዊነትም ውጭ ቢሆንም በ6 አመት ቆይታው ሁለት የሊግ እና አንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክብሮችን አሳክቷል፡፡

በግሉ በአውሮፓ ከተገኙ አፍሪካውያን ምርጥ መሆኑን ያስመሰከረው ፔሌ በ1992 የመጀመርያው የካፍ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጦ እንደነበርም ይታወሳል ። ጉዳዩን ሆን ብለው እንደፈጸሙት የተናገሩት እና ለሰሩት ሴራ የጥፋተኝነት ስሜት የማይሰማቸው በርናር ቴፒ ፤ ፔሌ ስሙን ይበልጥ ከፍ እንዲያደርግ እና የአውሮፓ ትልቁን ክብር እንዲያሳካ አድረጌዋለሁ በማለት እግር ኳስ ከእንዲህ አይነት ሴራ የጸዳ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ሰውየው ጉዳዩን አስበውበት መፈጸማቸውን ቢያምኑም የቀድሞው ኮከብ አብዲ ፔሌ ግን በድርጊቱ ተበሳጭቶ እንደነበር በአንድ ወቅት አክራ ውስጥ ከሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ ጋር በነበረው ቆይታ ይፋ አድርጓል።

የአንድሪ እና ጆርዳን አየው አባት አቢዲ ፔሌን ጉዳይ ጨምሮ በእግር ኳሱ ዙሪያ ለፈጸሟቸው ደባዎች የሁለት አመት እስር ተፈርዶባቸው የነበሩት አዛውንቱ ሰው ከ4 አመት በፊት ነበር ህይወታቸው ያለፈው፡

አንተነህ ሲሳይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top