ከአያት በተወረሰ ፍቅር ኢትዮጵያን የሚያገለግሉት ምሁር፦ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)

12 Hrs Ago 125
ከአያት በተወረሰ ፍቅር ኢትዮጵያን የሚያገለግሉት ምሁር፦ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)

ታዋቂ የማህበራዊ አንትሮፖሎጂስት እና ተመራማሪ ናቸው። በኢትዮጵያ እድገት፣ ባህላዊ ቅርሶች እና ማህበራዊ ሽግግር ላይ ባደረጉአቸው ሰፊ ጥናቶቻቸው ዕውቅናን አትርፈዋል።

የመልሶ ማቋቋም፣ የምግብ ዋስትና፣ ማህበራዊ ጥበቃ፣ ሀገር በቀል ዕውቀት እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታትን ጨምሮ የተለያዩ መስኮችን በጥናቶቻቸው በስፋት ዳስሰዋል።

አሉላ ፓንክረስት(ዶ/ር) የተወለዱት በአውሮፓውያኑ 1962 በኢትዮጵያ ነው። አባታቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ህይወታቸውን ሙሉ ለኢትዮጵያ የሰጡት የሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ ናቸው። እንዲሁም በጣሊያን ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ በመወገን ጠንካራ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ዝነኛ ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋቿ ሲልቪያ ፓንክረስት አያታቸው ናቸው። ቤተሰቦቻቸው ለኢትዮጵያ ያላቸው ጥልቅ ፍቅር በትምህርታቸው ምርጫ ላይ ጭምር ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ ጥናታዊ ሥራዎችን በማሳተም ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በተለይም ፍልሰት በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ላይ የሚያሳድረውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችን የሚያብራሩ ሥራዎችን አበርክተዋል።

ሌላው አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ያተኮሩባቸው ዘርፎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መካከል ባህላዊ የግጭት ሂደቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሥራዎቻቸውም ሀገር በቀል የችግር አፈታት ዘዴ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን እና በየአካባቢው የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ አስፈላጊ መሆናቸውን አሳይተዋል።

እንደ ፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም (PSNP) ባሉት እና ድህነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሠሩ ድርጅቶች ውስጥ አማካሪ እና ተመራማሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚያካሄዷቸው ጥናቶቹ ህብረተሰቡ በልማት ፕሮጀክቶች ተሳትፎ በባህል ውርሶች እና በዘላቂ ልማት መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያጎሉ ናቸው።

የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ሀገር በቀል ዕወቀቶችን እና የኢትዮጵያ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት በርካታ ተጨባጭ ሥራዎችን ሠርተዋል። ዘመናዊነትና ሉላዊነት በኢትዮጵያ ባህላዊ ማንነት ላይ ምን ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምርምሮችን ሠርተዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይም በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ከማሳተማቸውም በላይ መሬት ላይ አውርደው ተግባራዊ በማድረግ ረገድም ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ Ethiopian Society of Sociologists, Social Workers and Anthropologists (ESSSWA)፣Young Lives, a longitudinal study on childhood poverty in Ethiopia ባሉ ማኅበራዊ ጥበቃ እና በኅብረተሰብ ዕድገት ላይ አተኩረው በሚሠሩ የተመድ እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ ነው፡፡

አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በሥራዎቻቸው አማካኝነት የኢትዮጵያን ውስብስብ ማህበራዊ እና ባህላዊ ገጽታ ለመረዳት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። በሁለገብ የአንትሮፖሎጂ ዕውቀታቸው ታሪክ እና ባህልን ለልማት በማዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳዩ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ምሁራንን አነቃቅተዋል፡፡ ምሁራዊ ሥራዎቻቸው በማህበራዊ አንትሮፖሎጂ መስኮች ዙሪያ ያተኮሩ ሲሆን፣ የልማት ተግዳሮቶች እና ልማዳዊ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።  

በ1970ዎቹ በደርግ መንግሥት ሲደረግ የነበረውን የገጠሩን የሰፈራ ፕሮግራም እንቅስቃሴ ያስከተለውን ተፅዕኖ በስፋት መርምረዋል። በዚህም ሰዎች ከነበሩበት አካባቢ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚፈጠርባቸው፣ የባህል እና ማንነት ግጭት እንደሚኖር፣ በሰፈሩባቸው አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ሰፋሪዎቹን ለማላማድ ዳተኛ መሆናቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

ጥናቶቻቸውን የሚሠሩት በአካል ማኅበረሰቡ ውስጥ ሆነው በመሆኑ እንደ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት፣ የጉራጌ ያጆካ እና ሌሎች ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል የሚያሳይ ተጨባጭ ጥናትም ይፋ አድርገዋል፡፡

ማኅበራዊ ጥበቃና ደህንነት ሌላው በትኩረት የሚሠሩበት ዘርፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና መርሐ ግብር የሆነው ሴፍቲ ኔት ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በዚህም እጅ አጠር ሰዎች ከድህነት የሚያስወጣቸውን አቅም እንዲፈጥሩ በትኩረት ሠርተዋል። የወጣት ህይወት ፕሮጀክት አካል በመሆንም በኢትዮጵያ ህፃናት መካከል የትምህርት፣ የተመጣጠነ ምግብ እና በአጠቃላይ ደህንነት ላይ የሚታየው ልዩነት በትውልድ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በማጥናት ክፍተቱን ለማጥበብ እየሠሩ ይገኛሉ።

የዳበሩ ባህላዊ ዕውቀቶች በሥርዓት ተጠብቀው እንዲቆዩ በአጽንኦት ይሠራሉ፡፡ በዚህም በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ዕውቀቶች አስፈላጊነት እና ዋጋ፣ ሉላዊነት እና የከተሞች መስፋፋት በኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ላይ እያስከተሉ ባሉት ተፅዕኖዎች፣ በማህበረሰብ ተሳትፎ እና በመንግስት ፖሊሲዎች አማካኝነት ባህላዊ ሀብቶችን እና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን መጠበቅ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያለ ዕረፍት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የአሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፍቅር ከአያት የተወረሰ ነው፡፡ አያታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት የጣሊያንን የግፍ ወረራ ለዓለም ማኅበረሰብ ያጋለጡ ብርቱ የኢትዮጵያ ጠበቃ ነበሩ፡፡ "New Times and Ethiopia News" የተባላ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩት ሲልቪያ ፓንክረስት በዚህ ጋዜጣ ስለኢትዮጵያ በግፍ መወረር እና ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው እያደረጉ የነበረውን እንቅስቃሴ ሰፊ ሽፋን ይሰጡ ነበረ፡፡ ጥረታቸውን ያደንቁ የነበሩት አጼ ኃይለሥላሴም ጣሊያን ተሸንፋ ከኢትዮጵያ ከተባረረች በኋላ አመስግነዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም በአርበኝነት የተጋደሉላት ውድ ሀገራቸው እንደሆነች አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ሲልቪያም ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በመምጣት ቀሪ ህይወታቸውን በኢትዮጵያ በመኖር በክብር አርፈዋል፡፡ አርበኛዋ ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፉም በቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የክብር ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡

የሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም እናታቸውን ተከትለው መጥተው ለኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ኖረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ፍቅራቸው የተነሳም ልጃቸውን በኢትዮጵያዊ ጀግና ራስ አሉላ አባነጋ ስም አሉላ ብለው ሰይመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ዕሜያቸውን ለኢትየጵያ እና ለኢትዮጵያ ታሪክ ሰጥተው ኢትዮጵያን አገልግለው ከእናታቸው ጎን አርፈዋል፡፡ "The Ethiopian Borderlands"፣  "The History of Ethiopian Towns"፣ "Economic History of Ethiopia, 1800-1935" እና ሌሎች የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮሩ መጽሐፍትን አሳትመዋል፡፡ የአክሱም ሀውልትን ጨምሮ በእንግሊዝ እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶችን አስመልሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከማስተማራቸውም ባሻገር የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት (IES) መሥራች ነበሩ፡፡

ለዚህም ነው የዛሬው ባለታሪካችን እና ልጃቸው አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በአባታቸው ቀብር ዕለት “አባቴ ከእግዚአብሄር የተሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማገልገል ነበር” ያሉት፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጆቻቸውን ሲያሳድጉም በኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ፍቅር ኮትኩተው ነው፡፡ ይህንንም አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)፣ "ሲያሳድገን ለኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ ያለውን አክብሮት አስተላልፎልናል። እኔን አሉላ ብሎ ሲሰይመኝ እህቴን ደግሞ ታሪክ ብሎ ስም አወጣላት። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ በኃያላን ቅኝ ገዥ ሀገራት የተዘረፉ ቅርሶችን በተለይ ታቦታት መስቀሎችን ብራና ለማስመለስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ ነበር" በማለት አረጋግጠዋል፡፡

አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) የአባት እና የአያታቸውን ፈለግ በመከተል ነው ሙሉ ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ጥናት ላይ ያደረጉት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ተዘርፈው ወደ እንግሊዝ ሀገር የሄዱ ቅርሶችን በሚያስመልስ ኮሚቴም ውስጥ አባል ሆነው ብዙ ቅርሶች እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ በጥናታቸው ገጠራማዋ ኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩሩት አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) የሕዝቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ጥናቶችን እና መጣጥፎችን አሳትመዋል፡፡ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ንባብ ማኅብረሰብን እንደሚያንጽ ያምናሉ፡፡ አንባቢ ትውልድ ለማፍራትም የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ ንባብ እየተዘነጋ መምጣቱን እና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ፣ "በአሁኑ ወቅት በሞባይላችን በምንደቀንበት ዘመን ለንባብ የነበረንን ፍቅር ለቀጣይ ትውልድ ካላስተላለፍን ማኅበረሰባችን ምን ዋጋ እና ተስፋ ይኖረዋል?" በማለት ይጠይቃሉ፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top