የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሃገሪቱ የሚተገበር እና 500 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል የተባለውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል፡፡
ስታርጌት የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት የተለያዩ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በጋራ የሚተገብሩት ነው ተብሏል፡፡
በግሉ ዘርፍ ያሉ ተቋማት ኢንቨስት የሚያደርጉበት ይህ ፕሮጀክት አሜሪካ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመሠረተ ልማት ዘርፍ በተፎካካሪ አገሮች ላይ ከፍተኛ ብልጫ እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፕሮጀክቱን በኋይት ሀውስ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ስታርጌት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ታሪክ እጅግ ትልቁ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ሃሳብ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት እንደተጀመረ የተገለፀ ሲሆን፤ አሁን ላይ ለስራው ማስኬጃ 100 ቢሊየን ዶላር መመደቡ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የተቀረው ገንዘብ ደግሞ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ስራ ላይ እንደሚውል እና ወደ 100 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል።
ፕሮጀክቱ በኦፕን ኤኣይ፣ ኦራክል፣ በጃፓኑ ሶፍትባንክ እንዲሁም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስት የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ተቋም በትብብር እንደሚከናወንም ነው የተገለጸው፡፡
በሜሮን ንብረት