የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የእቅድ አፈፃፀም የስትሪንግ ኮሚቴ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፤ የኢትዮጵያ ታምርት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በተለያየ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ከ625 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
የአምራች ኢንዲስትሪዎች የማምረት አጠቃቀም 46 በመቶ የነበረ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ፤ ንቅናቄው ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ያለበት ደረጃ በአማካይ የማምረት አጠቃቀም ወደ 61 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከላይ እስከታች ባለው የመንግስት አመራር ትኩረት እንዲሰጠው ማስቻሉን ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
በዘርፉ ችግሮች ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ውይይት በማድረግ ለችግሮቹ የመፍትሔ ባለቤት በመሆን በጋራ መስራት በመቻሉ የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት፣ በራስ ምርት የመኩራትና የመጠቀም ባህላችን እየተሻሻለ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
በውይይት መርሃ ግብሩ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈፃፀም እየቀረበ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።