"በእግር ኳሱ በ63 ዓመት ውስጥ ምን እንደሰራን አለማጥናታችን አንዱ ችግር ነው" - ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር

14 Hrs Ago 79
"በእግር ኳሱ በ63 ዓመት ውስጥ ምን እንደሰራን አለማጥናታችን አንዱ ችግር ነው" - ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር

ልክ በዛሬዋ ዕለት ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችበት ቀን ነው።

የዚህን ታሪካዊ ቀን 63ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ "አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን እንዴት እንገንባ?" በሚል ርዕስ ኢቢሲ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በውይይት መድረክ ላይ አስተያየቱን የሰጠው የስፖርት ዞን ፕሮግራም አዘጋጅ ሰኢድ ኪያር ለበርካታ ዓመታት ምን እንደተሰራ አለመጠናቱ አንዱ ችግር መሆኑን ተናግሯል።

ችግሮቹን በዋናነት በሶስት መልኩ ከፋፍሎ እንደሚመለከተው ገልፆ ከአለመጠናቱ ባሻገርም ያለንን ነገር አለማወቅ እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኑን ለመቼ ነው መገንባት የታሰበው የሚለው መታየት እንዳለበት ጠቁሟል።

በአስተዳደር በኩል ለሚነሳው ጥያቄ የይድነቃቸው ተሰማን የስኬት ጊዜ አንስቶ፤ ሆኖም ያኔም ውጤታማ ያልነበርንባቸው ጊዜዎች ስለነበሩ ከዛኛው ይልቅ ያለንን አቅም መመልከት ላይ ማተኮር የተሻለ ነው ሲል ተናግሯል። 

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በበኩላቸው፤ እግርኳሱን ስለከበቡት በርከት ያሉ ችግሮች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ለችግሩ መፍትሄ እንዲሆን ችግሩን ጠንቅቆ ማወቅ ግማሽ እርምጃ እንደሆነ ያመላከቱት ዮሀንስ ሳህሌ፤ የጠንካራ ሊግ አለመኖር፣ ደካማ ተጫዋቾች ምልመላ ሂደት፣ ጥራት ያለው ዘመናዊ ስልጠና አለመኖር፣ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት እንዲሁም የአስተዳደር እና አመራሮች ብቃት ማነስ እንደ ችግር የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በፓናል ውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ሳሙኤል ስለሺ በበኩላቸው፤ ለእግርኳሱ እና ለብሄራዊ ቡድኑ ደካማ ውጤት ምክነያት ክለቦች ናቸው ብለዋል።

ክለቦች ጠንካራ እና ውጤታማ ከሆኑ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እና ጠንካራ እግርኳስ ይኖረናል ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ እግርኳስን እንደ ልማት አና ኢንደስትሪ ወስዶ መስራት እንደሚያስፈልግና በተለይም በክለቦች ላይ ትኩረት አድርጎ ማስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀዋርያው ጴጥሮስ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top