ባለፉት 6 ዓመታት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በተደረጉ የሕግ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ በፍትሕ ዘርፉ መሰረታዊ ለውጦችና ስኬቶች መመዝገባቸውን የፍትሕ ሚኒስትር ወ/ሮ ሃና አርዓያሥላሴ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ በፍትሕ ዘርፉ የተተገበሩ የሪፎርም ስራዎችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር በዘርፉ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ማሻሻያ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ከተሻሻሉ ሕጎች መካከል ለብዙ ቅሬታዎች ምንጭ የነበረውን የሽብር ሕግ በማስተካከልና በማሻሻል የግለሰብ መብቶችን ባስከበረ እና የአስፈጻሚ ተቋማትን ተጠያቂነት ባረጋገጠ መልኩ ታይቶ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።
አዲስ የምህረት ሥነ ሥርዓት ሕግ ማውጣት መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ለውጡን ተከትሎ በወንጀል አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ክስ ላይ ያሉ ጉዳዮች ታይተው በሕጉ ላይ ያለውን ሥርዓት ተከትሎ በመሰራቱ 40 ሺህ ሰዎች በምህረትና በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉን አንስተዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው ሕግ እና የሚዲያ ሕጉን በማሻሻል የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ዜጎች በተለያየ መልኩ ተደራጅተው በሀገራዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉባቸውን መሰረቶች መጣል ተችሏል ነው ያሉት።
ከእነዚህ መካከል የንግድ ሕጉ ለ50 ዓመታት የቆየ ዘመናዊ ንግድና ኢንቨስትመንትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነበር ያሉት የፍትሕ ሚኒስትሯ ፤ የንግድ ሕጉን ለማሻሻል ሰፋ ያሉ የምሁራን ውይይቶች ተደርገው በአዲስ መልኩ ማውጣት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ በመሆኑም በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚተገበሩ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
የግልግል ዳኝነትን የሚመራ አዲስ የዳኝነት ሕግ መውጣቱን አውስተው፤ ከዚህ በፊት በግልግል ዳኝነት እርቅ የሚፈጸሚበት ሕግ አልነበረም ብለዋል።
በመሆኑም አሁን በፍርድ ቤቶች ያለውን ዳኝነት ጫና ለመቀነስ የግልግል ዳኝነት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
ሙያና ሙያተኞች እንዲያድጉ የጠበቆች ማህበር ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል የጠበቆች አስተዳደርን የተመለከተ አዲስ ሕግ መውጣቱንም አክለዋል።
ታራሚዎችን ማረምና ማነጽ የሚያስችል፣ ተመልሰውም ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር አዲስ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕግ መውጣቱንም ጠቅሰዋል።
የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕጉም እንደዚሁ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ በመሆኑ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ላለው የፍትህ አስተዳደር አመቺ የሆነ ሕግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለማጽደቅ በሂደት ላይ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።