ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት፡- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

5 Days Ago 137
ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት፡- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገልጸዋል።
 
ሚኒስትር ዴኤታው የጃፓን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ሺሚዙ ሺንሱኬ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
 
ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ላላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ በውይይታቸው ገልጸዋል።
 
አምባሳደር ምስጋኑ ለልዩ ልዑኩ በጃፓን ለተካሄደው ስኬታማ የጃፓን አፍሪካ ልማት ፎረም (ቲካድ) ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
 
መንግስት ኢትዮጵያ ቲካድ እና ሌሎች የሁለትዮሽ ትብብር አማራጮችን በመጠቀም ከጃፓን ጋር በንግድ እና የግሉ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የጃፓን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ሺሚዙ ሺንሱኬ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት በጃፓን ከተካሄደው የቲካድ ፎረም ጎን ለጎን ያደረጓቸውን የሁለትዮሽ ምክክሮች አድንቀዋል።
 
ልዩ ልዑኩ በሱዳን ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ከአምባሳደር ምስጋኑ ጋር የተወያየ ሲሆን፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሰሉ ቀጣናዊ ተቋማት ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ ለማምጣት መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
 
በተጨማሪም ሁለቱም ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top