በሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠሩት የፈርስት ግሎባል ቡድን አባላት

13 Hrs Ago 188
በሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠሩት የፈርስት ግሎባል ቡድን አባላት

ተማሪዎች የሳይንስ የቴክኖሎጂ የኢንጂነሪንግ እና የሂሳብ እውቀትን በመጠቀም ለአሁናዊ  የዓለም ችግሮች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም መፍትሄ እንዲያመነጩ የተለያዩ እድሎች ይፈጠራሉ፡፡ 

እድሎችን በመጠቀም የራሳቸውን የቤተሰባቸውን የአከባቢያቸውን የሀገራቸውን እንዲሁም በዓለም ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ ያፈላልጋሉ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ190 ሀገራት በላይ የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር በቅርቡ በግሪክ አቴንስ ታካሂዷል፡፡

7 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የፈርስት ግሎባል ቡድን በውድድሩ ተሳትፎ ከዓለም 2ኛ ደረጃ በመያዝ የብር ሜዳልያ ተሸልሟል፤ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ስሟን ማስጠራት ችሏል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የሶፎትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዳግማዊ ግሩም የቡድኑ መሪ ሲሆን ስለ ውድድሩ ሲናገር የዘንድሮው ውድድር ትኩረት የወፊቷን ዓለም መመገብ (Feed The Future) የሚል ቻሌንጅ ነበር፡፡

የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምግብ ከማምረት እስከ ማጓጓዝ ያለውን ሂደት እንዴት በቴክኖሎጂ መስራት ይቻላል የሚለውን የመፍትሄ ሀሳብ ማስተማሪያ ሮቦቲክስ መስራት ለሁሉም ተወዳዳሪዎች የቀረበ ፈተና እንደነበር ይናገራል፡፡

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (ሮቦቶችን) በመጠቀም እንዴት ምግብ መማረት እንደሚቻል፤ የተመረተውን ምግብ ወደ ማከማቻ መጋዘን እንዴት ማጓጓዝ ይቻላል? ሮቦቶችን በመጠቀም በግብርን ስራ ላይ የተሻለ ምርታማ መሆን ብቻ ሳይሆን የተመረተውን ምግብ   ወደ መጋዘን በአግባቡ ማጓጓዝ ይቻላል የሚለውን በቴክኖሎጂ አስተማሪ ሮቦት መስራት በመቻላችን 2ኛ ደረጃ መያዝ ችለናል ብሏል፡፡

ከ100 በላይ ኪቶች ያሉት ሮቦት ተበታትኖ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ተላከልን፤ስራውና ዓላማው አንድ የሆነ ሮቦት ዲዛይን እንድንሰራ ቻሌንጅ ተሰጠን፤ የተላከውን የሮቦት ኪት በመጠቀም በውድድሩ ለማሸነፍ የተሻለና የተለያዩ ዲዛይን በመምጥ ዓላማውን ማሳካት የሚችል ሮቦት መስራት መቻላቸውን ይናገራል ወጣት ዳግማዊ፡፡

 

የ18 ዓመቷ ወጣት ፅዮን ፍፁም ከሳፋሪ አካዳሚ የተገኘች የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት፡፡“ውድድሩ አድካሚ ነበር፡፡ መጀመሪያ አከባቢ ባጋጠመን የቴክኒክ ችግር ጥሩ መጫወት ባንችልም ችግሩ ተስተካክሎ በጥሩ ሁኔታ መጫወት ችለናል፤በልምምድ የሰራናውን በውድድሩ በመድገም ጥሩ ውጤት ማሳየት በመቻላችን 2ኛ ደረጃ መውጣት ችለናል፡፡” ብላለች፡፡

“ሀገራችንን ወክለን በውድድሩ 2ኛ ደረጃ መውጣታችን ስነገረን በጣም ደስተኞች ነበርን፡፡ይህም ደስ የሚል ትልቅ ስሜት ፈጥሮብናል፡፡ በሮቦቲክስ ውድድሩ ከዓለም 2ኛ ደረጃ በመውጣት ያገኘነው ትልቁ ሽልማታችን የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ በስፍራው ማውለብለብ ፤ሀገራችንን በዓለም መድረክ ስሟን ማስጠራት መቻላችን ነው” ብላለች፡፡

ወደፊት ብዙ ሰርታ በውድድሮች በመሳተፍ ሀገሯን ዳግም ማስጠራት እፈልጋለሁ የምትለው ታዳጊዋ በኢትዮጵያ  ስለሮቦቲክስ ያለው አመለካከት እየተሸሻለ ቢሆንም አሁን ሰፊ ክተቶች አሉ ባይ ናት፡፡ ለዘርፉ ተገቢ ትኩረት መስጠት ከተቻለ ወደፊት የተሻለ ውጤት መምጣት እንደሚቻልም ታምናለች፡፡ ት/ቤቶች፤ መንግስት ለሮቦቶክስ ቴክኖሎጂ ምቹ አውድ ቢፈጠሩ ብቃት ያላቸው ታዳጊዎችን  ማፍራት ይቻላል ብላለች፡፡

ኖህ ጌታቸው በአደማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የ4ኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪና የፈረስት ግሎባል ቡድን የቴክኒካ ቡድን መሪ ነው፡፡ ከህፃንነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ ለፈጠራ ፍላጎት ያለው ሲሆን ከተሳተፉ 7 አባላት አንዱ ነው፡፡

ስለ ውደድሩ ሲናገር “አራት ኳስ መያዝ የሚችል ሮቦት መስራት ችለናል፡፡ እኛ ማሸነፍ የቻልነው  ሆልሞኒክ ድራይቭ የሚባለውን ማለትም የሰራነው ሮቦት እየሄደ እያለ ወደ ፈለገው አቅጣጫ መዞር ሲፈልግ ወዲያው መዞርና ወደ ሁለም አቅጣጫ መሄድ አንዲችል አድርገን ነው የሰራነው፤ በዚህም ጊዜ መቆጠብ ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ ሌሎች  ተፎካካሪዎች የሰሩት ሮቦት 2 ኳስ ነበር የሚይዘው እኛ ግን በአንዴ 4 ኳስ መያዝ የሚችልና  ዓላመውን ማሳካት የሚችል አስተማሪ ሮቦት ሰርተናል ፡፡ ይህም እንድናሸንፍ መጣም አግዞናል” ብሏል፡፡

በሮቦቲክስ ውድድሩ ከዓለም 2ኛ ደረጃ በመውጣት ያገኘነው ትልቁ ሽልማታችን የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ በስፍራው ማውለብለብ ፤ሀገራችንን በዓለም መድረክ ስሟን ማስጠራት መቻላችን ነው ሲሉ የፈረስት ግሎባል ቡድን አባላት ተናግረዋል፡፡

በአቴንስ በነበራቸው ቆይታ ከ30 ሀገራት 12 ጨዋታዎችን ማድረጋቸውን፤የፈጠራ አቅማቸውን፤ የተግባቦት ክህሎታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን የሚናገሩት የቡድኑ አባላት ወደፊት የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ እና የሕሳብ እውቀትን አጣምሮ በመጠቀም ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ ዓላማቸው መሆኑን ታናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተስጥኦና ፍላጎት እያላቸው ግን እድል ያላገኙ ወጣቶች ብዙ ናቸው፤ ለእነዚህ እድል መፍጠር እቅማቸውን በማውጣት ለችግሮች መፍትሄ እንዲዘይዱ፤ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች መስራት እንደምንችል ለማሳየት የጀመርናቸውን ጥረቶች  ወደፊት አጠናክረን እንቀጥላለን  ብለዋል፡፡

ሮቦቱ ውስብስብ ቢመስልም ፍላጎት ካለ፤ ትኩረት መስጠት  ከተቻለ አይከብድም፡፡ ወደፊት በኢትዮጵያ ሮቦቲክስን ማስፋፋት በውድድሮች ማሳተፍ፤ሰው ሰራሸ አስተውሎትን እውቀት የሚጠይቅ ስለሆን ፍላጎት ላላቸው ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር ጥሪ ነው የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሮቦት ሲባል የመጫወቻ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ስለ ሮቦቲክስ ያለው ግንዛቤ አነተስኛ ነው፡፡ ሮቦቲክስ ሰዎች እንደሚያስቡት መጫወቻ ሳይሆን ትልቅ ችግር ፈቺ የሆነ ኃላፊነት የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ስለ ሮቦቶ ሁሉም ሰው ትክክለኛ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል፡፡  መንግስትም ለዘርፉ እድገት የጀመራቸውን የመሰረት ልማት ግንባታ  አጣናክሮ ከቀጠለ  ወደፊት የተሻለ ውጤት መምጣት ይቻላል  ብለዋል የቡድኑ አባላት፡፡

በላሉ ኢታላ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top