ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ሥራ ህብረተሰቡን እና ባለሀብቱን በማሳተፍ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ካዛንቺስ አካባቢ ካሉ ባለሐብቶች ጋር አካባቢውን በትብብር መልሶ ማልማት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ በተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ እንደ መጀመሪያው ሁሉ የሁለተኛውንም የኮሪደር ልማት ስራ ህብረተሰቡን እና ባለሀብቱን በማሳተፍ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የካዛንቺስ አካባቢ ባለሐብቶች በበኩላቸው፤ በኮሪደር ልማት እና በመልሶ ማልማት ስራው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የከተማው ጽዳትና ውበት ለኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚችሉት ሁሉ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም አካባቢውን እንደሚያለሙ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ባለሐብቶች ያሏቸውን የልማት ጥያቄዎች በማቅረብ ለመልሶ ማልማት ሥራው በቀረበላቸው ጥሪ ደስተኛ መሆናቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።